AMN ጥር 16/2018
በኅብር ሠርተን፣ አዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕያችንን ዳር እናደርሳለን ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ ማለዳ የከተማችንን የ6 ወራት የሥራ ጉዞ የምንመዝንበትን የግምገማ መድረክ በይፋ ጀምረናል ብለዋል።
በዚህ የሦስት ቀን መርሃ ግብር፣ በ2018 በጀት ዓመት አጋማሽ በመንግሥትና በፓርቲ ሥራዎች የተከናወኑ አበይት ተግባራትን፣ ከወረዳ እስከ ከተማ አስተዳደር ካለው አመራራችን ጋር በዝርዝር እንገመግማለን።
ባለፉት 6 ወራት፣ በ24/7 (ሃያ አራት ሰባት) የተለወጠ የሥራ ባህል፣ ነዋሪዎችንና የልማት አጋሮችን አስተባብረን በሁሉም ዘርፎች ያቀድናቸውን ሥራዎች በአማካይ 95.3 % ማሳካት ችለናል ብለዋል።
ምንም እንኳን የላቀ ውጤት ብናስመዘግብም፣ የታዩ ጉድለቶችንና የተቋማትን ወጥ ያልሆነ የእቅድ አፈጻጸም፣ በተለይም ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሉ ክፍተቶችን፣ አገልግሎት ለመስጠት ጉቦ መጠየቅን፣ የቅንነት መጓደልን በግልጽ በመለየት ለማረም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን የምናስቀምጥበት፤ ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት ተጨማሪ አቅምና ተሞክሮ የምንሰንቅበት እንዲሁም የከተማችንን ነዋሪዎች በተሻለ ትጋትና ታማኝነት ለማገልገል የምንዘጋጅበት መድረክ ይሆናል።
ይህ ውጤት እንዲመዘገብ የተጋችሁ፤ የደከማችሁ መላው አመራሮቻችንን እና ሰራተኞችን እንዲሁም ያገዛችሁን የልማት አጋሮችን ከልብ አናመሰግናለን።
በኅብር ሠርተን፣ አዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕያችንን ዳር እናደርሳለን ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መልዕክት አስተላልፈዋል።