AMN- ጥር 16/2018
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ አየር ኃይል የተመሠረተበትን 90ኛ ዓመት በዓል አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ተቋሙ ላለፉት ዘጠኝ አሰርት ዓመታት የሀገርን ሉዓላዊነት በማስጠበቅና የኢትዮጵያን ጠላቶች በመመከት ረገድ የላቀ ሚና ማበርከቱን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አየር ኃይሉ በታሪኩ በርካታ ውጣ ውረዶችን ቢያልፍም፣ ዛሬ ላይ ከመቼውም ጊዜ በላይ የላቀ ብቃትና የቴክኖሎጂ ቁመና ላይ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።
አየር ኃይሉ የኢትዮጵያን ዳርቻ ከማስከበር ባለፈ ለአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ትልቅ አስተዋጽዖ ማድረጉን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተለይም በታንዛንያ የአየር ክልል ጥበቃና በተለያዩ ሀገራት በሚከናወኑ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የነበረው ተሳትፎ ተቋሙን የአሕጉሪቱ ኩራት እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ጥቅም ማስከበር የኢትዮጵያውያን ግዴታ ሲሆን፣ የወዳጆቻችን ደግሞ የፈቃድ ድጋፍ ነው፤ ስለዚህ ጥቅማችንን ለማረጋገጥ ቀዳሚዎቹ እኛው መሆን አለብን ብለዋል።
እኛ ያለኢትዮጵያ ሌላ እናት የለንም፤ ኢትዮጵያም ያለ እኛ ልጆች የላትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዜጎች በከፍታም ሆነ በዝቅታ ጊዜያት ከሀገራቸው ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
በተቋሙ ውስጥ የታዩ ስኬቶች የበርካታ ጀግኖች ድምር ውጤት መሆናቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እንደ ጀነራል ለገሰ ተፈራ፣ ጀነራል አሸናፊ ወልደጻዲቅ፣ ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ : ኮሎኔል ባጫ ሁንዴ እና የዛሬው አየር ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ ያሉ ጀግኖችን በማንስት ክብራቸውን ገልጸዋል።
ወደፊትም ተቋሙ ይበልጥ እንዲጠናከር በቴክኖሎጂ ብቻ ሳይሆን በሰው ኃይል ግንባታ ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረው፣ የበቃ የሰው ኃይል ከሌለ ማሽኑ ብቻውን ውጤት ሊያመጣ አይችልም ብለዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ