AMN ጥር 17/2018 ዓ.ም
ባንኮች ለተመረጡ የገቢ ዕቃዎች የብድር ሰነድ (Letters of Credit) ይሁን ሌላ ክፍያ መንገድ ሲፈቅዱ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ተመንን እንደ አመላካች ዋጋ እንዲጠቀሙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሐምሌ 2016 ዓ.ም ተግባራዊ ያደረገውን የውጭ ምንዛሪ መመሪያን ተከትሎ፣ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ እንዲወሰን መደረጉ ይታወቃል። መመሪያው ባንኮች ከደንበኞቻቸው ጋር በመደራደር የውጭ ምንዛሪ መሸጫ እና መግዣ ተመኖችን መወሰን እንዲችሉ ይፈቅዳል።
በተጨማሪም ባንኮች ቀደም ሲል ይጠቀሙበት የነበረው ዝቅተኛ የገቢ ዕቃዎች ዋጋ መመሪያ (Minimum Price Directive) በመሰረዙ፤ አሁን ግን በአዲሱ የውጭ ምንዛሪ መመሪያ መሠረት የገቢ የዕቃዎችን ዋጋ ትክክለኝነት የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባቸው።
ይሁን እንጂ፣ ባንኮች ለብድር ሰነድ (Letters of Credit) የሚጠቀሙባቸው ዋጋዎች ከኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የማጣቀሻ ዋጋዎች ጋር ሲነፃፀሩ ከፍተኛ ልዩነት እንዳላቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባደረገው ክትትል አረጋግጧል።
በመሆኑም የዋጋ ልዩነቶቹን ለማስተካከልና የዋጋ ማጣቀሻዎችን ለማጣጣም ሁሉም ባንኮች ከጥር 19 ቀን 2018 ዓ.ም (January 27, 2026) ጀምሮ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ተመንን እንደ አመላካች ዋጋ ይጠቀማሉ።
ይህም በባንክ ሥርዓቱ እና በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን መካከል ያለውን የዋጋ ልዩነት ለማስወገድ እና የውጭ ምንዛሪ መረጃዎችን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።