AMN ጥር 18/2018 ዓ.ም
በሞዛምቢክ ታይቶ የማይታወቅ ከባድ የጎርፍ አደጋ የተከሰተ ሲሆን፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት የመታደግ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
የብራዚል፣ የደቡብ አፍሪካ እና የእንግሊዝ የነፍስ አድን ቡድኖች በቦታው ተገኝተው የሕይወት አድን ተግባራትን እያከናወኑ ይገኛሉ።
የጎርፍ አደጋው የተከሰተው ኢንኮማቲ የተባለው ወንዝ ሞልቶ ግድቡን በመጣሱ እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪዎችና ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት በዋና ከተማዋ ማፑቶ አቅራቢያ የሚገኙ መንደሮች በውኃ ተጥለቅልቀዋል።
በአደጋው እስካሁን ድረስ የ12 ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን፣ በሀገሪቱ ከጥር ወር መጀመሪያ ጀምሮ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ ከ642 ሺህ በላይ ሰዎች ቤቶቻቸውን፣ የዳልጋ ከብቶቻቸውን እና የሩዝ ማሳዎቻቸውን ሙሉ በሙሉ ማጣታቸው ተገልጿል።
በአሁኑ ወቅት በማፑቶ እና በጋዛ ግዛቶች መካከል ያለው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ የታገደ ሲሆን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች አሁንም ከዓለም ተለይተው በውኃ መሃል ይገኛሉ።
የአካባቢው ባለሥልጣናት ዜጎች ከንብረት ይልቅ ለሕይወታቸው ቅድሚያ እንዲሰጡና አደገኛ ከሆኑ ቦታዎች ለቅቀው እንዲወጡ እያሳሰቡ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
በወንድማገኝ አሰፋ