AMN-ጥር 18/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ ለጽዳትና ውበት እንቅፋት የነበሩ ከ29 ሺህ በላይ ህገ-ወጥ የውጭ ማስታወቂያዎችን ማስነሳት መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ታደለ ደመኮ (ዶ/ር) ለአዲስ ሚዲያ ኤፍ ኤም 96.3 ራዲዮ እንደገለጹት፣ የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ ከተማዋን የሚያበላሹ የውጭ ማስታወቂያዎችን የማንሳትና በዘመናዊ የዲጂታል ማስታወቂያዎች የመተካት ተግባር በስፋት እየተከናወነ ይገኛል።

ባለፉት 6 ወራት ህግና ስርዓትን ባላከበሩ የቁጥጥር ባለሙያዎች እና አመራሮችን ጨምሮ የህንፃ ባለቤቶች፣ ተቋራጮች፣ አማካሪዎች እና የሪል ስቴት አልሚዎች ላይ በተወሰደ እርምጃ የ129 ሚሊየን ብር ቅጣት ተተቀጥተዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት ከ39 ሺህ በላይ ህንፃዎች ላይ የደህንነት ማስጠበቅ ስራ መከናወናቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ ግንባታ የሚያከናውኑ አካላት ህንፃዎችን በሽፋን ከልሎ መገንባት፣ ተረፈ ምርቶችን በአግባቡ ማስቀመጥና ማስወገድ እንዲሁም ለሰራተኞች ደህንነት ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የከተማዋን ውበትና የነዋሪዎችን ደህንነት ለመጠበቅ የሚከናወኑ የቁጥጥር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቋል።
በሽታሁን መንግስቴ