የማርበርግ ቫይረስ የተገታበት መንገድ ኢትዮጵያ ለድንገተኛ በሽታ የማይበገር የጤና ሥርዓት መገንባቷን ያሳያል – አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

You are currently viewing የማርበርግ ቫይረስ የተገታበት መንገድ ኢትዮጵያ ለድንገተኛ በሽታ የማይበገር የጤና ሥርዓት መገንባቷን ያሳያል – አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
  • Post category:ጤና

AMN ጥር 18/2018

የማርበርግ ቫይረስ ሥርጭት የተገታበት መንገድ ኢትዮጵያ ለድንገተኛ በሽታ የማይበገር የጤና ሥርዓት መገንባቷን እንደሚያሳይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወሰደችው የተቀናጀና አስቸኳይ ምላሽ አሰጣጥ ሥርዓት ቫይረሱን ማጥፋት ችላለች።

በዚህም ኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና አደጋን በመከላከል በጥቅምት ወር ተከስቶ የነበረውን የማርበርግ ቫይረስን ከወራት በኋላ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት መቻሏን ተከትሎ የዕውቅናና ምስጋና መርሃ ግብር ተካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎችና አምባሳደሮች ተገኝተዋል።

በዚሁ ጊዜ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ የማርበርግ ቫይረስ በሽታን በመከላከል የተገኘው ውጤት ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከቫይረሱ ነፃ የሆነችበት መንገድ የጤና ፖሊሲው ስኬት፣ የአመራር ቁርጠኝነትና ቅንጅት ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ዕውን ለማድረግ የዜጎች ጤና ጥበቃ ስራ ቀዳሚ ተግባር ተደርጎ እየተሰራበት መሆኑንም ተናግረዋል።

ሳይንሳዊ አሰራርን በመከተል ፈጣንና የተቀናጀ ምላሽ የተሰጠበት ሥርዓትም ኢትዮጵያን ከማርበርግ ቫይረስ ነፃ መሆን እንዳስቻለ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስን የተቆጣጠረችበት መንገድ ድንገተኛ የበሽታ ሥርጭትን የመከላከል አቅም ማጎልበቷን ያሳያል ብለዋል።

የፌደራልና የክልል ጤና ተቋማት እንዲሁም የጤና ሙያተኞች የማርበርግ ቫይረስን ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት ላበረከቱት በትብብር ላይ የተመሰረተ አስደናቂ ቅንጅት አፈ ጉባኤው አመስግነዋል።

በቀጣይም የማርበርግ ቫይረስ ሥርጭትን በመቆጣጠር ሂደት የተገኘውን አስደናቂ ውጤት በማላቅ የጤና ሥርዓቱን የማድረግ አቅምና የማዘመን ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review