AMN – ጥር 19/2018 ዓ.ም
በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ የመጠቀምና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን መከላከል የሚያስችል በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) የታገዘ ሥርዓት ለማልማት ስምምነት ተፈረመ።
ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) እና የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን አማረ ናቸው።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በዚህ ወቅት፤ ስምምነቱ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ የመጠቀምና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን ለመከላከል የሚያደረገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል፡፡
ሥርዓቱ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን መሰረት በማድረግ ረቂቅ ወንጀሎች ከመፈጸማቸው በፊት ማስቀረትና ችግሩ ሲፈጠር የከፋ ጉዳት ሳይደርስ በፍጥነት መፍታት የሚያስችል መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ይህን ሥርዓት ለማልማት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አውስተው፤ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የላቀ ሥራና በተያዘለት ጊዜ ሠርቶ ለማስረከብ ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡
የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን አማረ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ኅብረት እና የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ድርጊት ግብረ-ኃይል አባል እንደመሆኗ የፋይናንስ ወንጀል መረጃዎችን ከሌሎች ሀገራት ጋር እንደምትለዋወጥ ገልጸዋል፡፡
በዚህም በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ የመጠቀምና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎች ውስብስብና ድንበር ተሻጋሪ በመሆናቸው የቴክኖሎጂ ድጋፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የሥርዓቱ መልማት ውስብስብ የሆነውን ወንጀል ከሀገራት ጋር በትብብር ብሎም ከሕግ አስከባሪዎች ጋር በጋራ በመሥራት ከወንጀል ማትረፍ እንደማይቻል ለማሳየት እንደሚያግዝ አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ የመጠቀምና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን ለመከላከልና ደኅንነቷን ለማረጋገጥ ሥርዓት ማልማቷ ለብዙ የአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ ይሆናል ብለዋል ዘገባው የኢዜአ ነው፡፡