ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የተገነባዉን ዘመናዊ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የእንስሳት ተዋጽኦ ማቀዝቀዣ መጋዘን እና ሁለገብ ሕንፃ መርቀዉ ስራ አስጀመሩ

You are currently viewing ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የተገነባዉን ዘመናዊ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የእንስሳት ተዋጽኦ ማቀዝቀዣ መጋዘን እና ሁለገብ ሕንፃ መርቀዉ ስራ አስጀመሩ

AMN ጥር 19/2018 ዓ.ም

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ዛሬ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ጋር በመሆን፣ የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ያስገነባውን ዘመናዊ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የእንስሳት ተዋጽኦ ማቀዝቀዣ መጋዘን እና ሁለገብ ሕንፃ መርቀን በይፋ ሥራ አስጀምረናል ብለዋል፡፡

ይህ ከ11 ሺህ 400 ካሬ ሜትር በላይ በሆነ ቦታ ላይ ያረፈ እና በአገሪቱ በግዙፍነቱ ቀዳሚ የሆነ የማቀዝቀዣ መጋዘንና ሁለገብ ሕንፃ፤ ከምርት በኋላ የሚፈጠርን ብክነትና ብክለትን በማስቀረት፣ የገበያ ማረጋጋትን በመፍጠር እንዲሁም በአምራቹ የሚመረቱ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የእንስሳት ተዋጽኦዎች ተፈጥሯዊ ይዘታቸውን ጠብቀው ለሸማቹ ማህበረሰብ እና ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ በማድረግ ረገድ የላቀ ፋይዳ ይኖረዋል።

በተጨማሪም ሸማቹ ማህበረሰብ በተገቢ ዋጋ ትኩስ የግብርና ምርቶችን እንዲያገኝ የሚያስችል ሲሆን፤ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና የገበያ ሰንሰለቱን በማሳጠር ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

አስተዳደራችን ለግብርና ምርት ጥራትና ተወዳዳሪነት አስፈላጊ የሆነው ይህ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን አስፈላጊውን ይዞታ በማቅረብ ያደረገውን ድጋፍ በሌሎችም ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል እየገለጽኩ፤ ይህ በዘርፉ የአገራችንን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ ከፍተኛ አገራዊ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት እውን እንዲሆን አስተዋጽኦ ላደረጉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ተቋማት በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review