AMN ጥር 19/2018
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከህዝብ ቅሬታ የሚቀርብበትን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለመቅረፍ በ’መሶብ’ የአገልግሎት አሰጣጥ የ94 % የህዝብ እርካታ ማግኘት መጀመራችን ለቀጣይ ስራችን ትልቅ ስንቅ ነው ሲሉ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ”በትጋት አዲስ አበባን ወደ ላቀ ስኬት!” በሚል መሪ ሃሳብ ሲያካሂድ የነበረውን የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የመንግስትና የፓርቲ ስራዎች አፈፃፀም ግምገማ አጠናቋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በግምገማ መድረኩ ላይ እንደገለጹት የአገልግሎት አሠጣጥን በማዘመን ከህዝቡ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ለመፍታት በተደረገዉ ሥራ አመርቂ ዉጤት ተገኝቷል።
በከተማዋ የሚስተዋለውን የቅሬታ አፈታትና የአገልግሎት አሰጣጥ የበለጠ ግልፅና ተጠያቂነት የሰፈነበት ለማድረግ ከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶች መዘርጋቱን አንስተዋል።

ከንቲባዋ፣ለአብነትም ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር በመተባበር የሚቀርቡ እንደ አገልጋይ፣ ዋርካ እና እንጠያየቅ ፕሮግራሞች ከፍተኛ ለውጥ አምጥተዋል።
በሌላ በኩል ከባለድርሻ አካላትና ከሕዝቡ ጋር በመተባበር 13 ቢሊዮን ብር የሚገመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማበርከት ከፍተኛ የሕዝብ አጋርነት መታየቱን ገልጸዋል።
በበጀት አመቱ ስድስት ወራት የተገኙ አመርቂ ዉጤቶች የበለጠ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በትኩረት እንደሚሰራም አስገንዝበዋል።
በቀጣይ የኑሮ ውድነት ጫናን መቀነስና የቤት ግንባታን ማፋጠን፤ ሌብነትንና ብልሹ አሠራርን በዘመናዊ አሠራርና በሕዝብ ተሳትፎ ማምከን፤ የገቢ አሰባሰብን ማጠናከርና የመረጃ አያያዝን ስርዓትን ማዘመን በትኩረት የሚሰራባቸው ዘርፎች እንደሆኑም ከንቲባ አዳነች አቤቤ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
በአስማረ መኮንን