AMN- ጥር 20/2018 ዓ.ም
የአሜሪካው የቴክኖሎጂ ግዙፍ ኩባንያ አማዞን (AMAZON) በስህተት በተላከ ኢሜይል አዲስ ዓለም አቀፍ የሰራተኞች ቅነሳ ማድረጉን ለሰራተኞቹ አስታውቋል።
በአማዞን ዌብ ሰርቪስ (AWS) ከፍተኛ ምክትል ፕሬዝዳንት በሆኑት ኮሊን ኦብሪ የተፃፈው የኢ-ሜይል ረቂቅ፣ ማክሰኞ ዕለት በስህተት ከአንድ የስራ አስፈፃሚ ረዳት በተላከ የቀን መቁጠሪያ ጥሪ ውስጥ ተካቶ ለበርካታ የአማዞን ሰራተኞች ደርሷል።
በዚህ ኢ-ሜይል ላይ ኩባንያውን “ለማጠናከር” በሚል ጥረት በተጻፈ ረቂቅ ጽሁፍ በአሜሪካ ፣ ካናዳ እና ኮስታሪካ የሚገኙ በርካታ ሰራተኞች እንደሚቀነሱ ተገልጿል፡፡
የተላከዉ የኢ-ሜይል መልዕክት ወዲያውኑ የተሰረዘ ሲሆን፣ በስህተት የተጋራ እንደሆነ ተገልጿል።
የአማዞን ቃል አቀባይ ግን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።
ኢ-ሜይሉ የሰራተኞች ቅነሳ መኖሩን በግልጽ ቢያሳይም፣ ሰራተኞቹ ግን በይፋ አልተነገራቸውም፡፡
በኢ-ሜይል የተላከዉ መልእክትም ለደንበኞች ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት፤ ኩባንያውን ለማጠናከር፣ የአመራር እርከኖችን ለመቀነስ እና የስራ ባለቤትነትን ለመጨመር ቢሮክራሲን ማስወገድ የሚል ሃሳብ እንደያዘ ተገልጿል፡፡
“እንዲህ ያሉ ለውጦች በሁሉም ሰው ላይ ከባድ ናቸው። እነዚህ ውሳኔዎች አስቸጋሪ ቢሆኑም ድርጅታችንን እና የአማዞን ዌብ ሰርቪስን ለወደፊት ስኬት ለማዘጋጀት በጥንቃቄ የተደረጉ ናቸው” የሚል መልእክት አካቷል፡፡
አማዞን ባለፈው ጥቅምት ወር 14ሺህ ሰራተኞችን መቀነሱ ይታወሳል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የቀድሞ የተቋሙ ሰራተኛ እንደሚሉት፣ ይህ ሁለተኛው የቅነሳ ዙር በሰራተኞች ዘንድ ለሳምንታት ሲጠበቅ የነበረ ነው።
እንደ አማዞን፣ ሜታ፣ ጎግል እና ማይክሮሶፍት ያሉ ዋና ዋና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከ2022 ጀምሮ በየዓመቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞችን በመቀነስ ላይ ይገኛሉ።
እስካሁን በዚህ ዓመት የፌስቡክ ባለቤት የሆነው ሜታ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞችን መቀነሱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ