በዋትሳፕ፣ በቴሌግራም እና በሌሎች የመልዕክት መላላኪያ ፕላትፎርሞች የሳይበር ጥቃቶችን የሚፈፀም መሆኑን ያውቃሉ ታዲያ ሊወሰድ የሚገባ የጥንቃቄ ምን እንደሆነ ያውቃሉ ?

You are currently viewing በዋትሳፕ፣ በቴሌግራም እና በሌሎች የመልዕክት መላላኪያ ፕላትፎርሞች የሳይበር ጥቃቶችን የሚፈፀም መሆኑን ያውቃሉ ታዲያ ሊወሰድ የሚገባ የጥንቃቄ ምን እንደሆነ ያውቃሉ ?

AMN – ጥር 20/2018 ዓ.ም

በዋትሳፕ፣ በቴሌግራም እና በሌሎች የመልዕክት መላላኪያ ፕላትፎርሞች የሳይበር ጥቃቶችን የሚፈፀም መሆኑን ያውቃሉ ታዲያ ሊወሰድ የሚገባ የጥንቃቄ ምን እንደሆነ ያውቃሉ ? የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ሊደረጉ የሚገባቸውን ጥንቃቄ አስመልክቶ የላከውን መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል ።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ)፤ በሀገራችን የዲጂታል ትስስር መስፋፋትን ተከትሎ በዋትሳፕ (WhatsApp)፣ በቴሌግራም (Telegram) እና በሌሎች የመልዕክት መላላኪያ ፕላትፎርሞች አማካኝነት በዜጎች ላይ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶችና የማጭበርበር ድርጊቶች በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመሩ መምጣታቸዉን በተለያዩ መንገዶች ማረጋገጥችሏል።

በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የሚካሄዱ የተለያዩ ሲምፖዚየሞችን፣ ዓለም አቀፍ መድረኮችን እና የኦንላይን ስብሰባዎችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ የሳይበር ወንጀለኞች የእነዚህን ኩነቶች ስም ለሀሰተኛ ድርጊቶቻቸው መጠቀሚያ እያደረጉት ይገኛሉ።

እነዚህ አካላት የማህበረሰቡን የግል መረጃ ለመስረቅ፣ የባንክ ሂሳቦችን ለመመዝበር እና የዲጂታል ደህንነትን ለማናጋት በተቀናጀ መልኩ እየሰሩ መሆኑን አስተዳደሩ በክትትልና በምርመራ አረጋግጧል።

እነዚህ የሳይበር ጥቃቶች የሚፈጸሙት ማህበረሰቡ ትኩረት የሚሰጣቸውን “ተፈላጊ” እና “ወቅታዊ” የሆኑ ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ በተዘረጋ ስልታዊ የማታለያ ዘዴ ነው።

አጭበርባሪዎቹ “ለሲምፖዚየሙ ተሳታፊዎች የተዘጋጀ ነጻ የኢንተርኔት ፓኬጅ”፣ “ልዩ የስራ ቅጥር” ወይም “ይህ የስብሰባ መሳተፊያ ሊንክ ነው፤ ከፍተው ይግቡ” የሚሉ አሳሳችና ማራኪ መልዕክቶችን በማሰራጨት ተጠቃሚዎች በመልዕክቱ ውስጥ የተካተተውን ሊንክ (Link) እንዲጫኑ ያደርጋሉ።

ይህ ድርጊት ተጠቃሚው ሳያውቀው ወደ አጥፊ ተልዕኮ ወዳላቸዉ ድረ-ገጾች እንዲያመራና ለጥቃት ተጋላጭ እንዲሆን የሚያደርግ የመጀመሪያው የወንጀለኞች እርምጃ እንደሆነ አስተዳደሩ ይገልጻል።

ጥቃት አድራሾቹ የአንዳንድ ግለሰቦች የግንዛቤ እጥረትና ትኩረት ማጣት የተነሳ የሚላኩላቸውን ሊንኮችና መልዕክቶች በጥንቃቄ የመመርመር ዕድላቸው አነስተኛ መሆኑን ተከትሎ ወንጀለኞቹ ይህን ሁኔታ እንደ ምቹ አጋጣሚ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።

ይህ አይነቱ ጥቃት ከግለሰቦች መረጃ ስርቆት ባለፈ፣ በእጃቸው የሚገኙ ሚስጥራዊ መረጃዎች በጠላፊዎች እጅ እንዲወድቁ በማድረግ በሀገር ደህንነትና ሉዓላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ የሚጋርጥ መሆኑን አስተዳደሩ በጥብቅ ያሳስባል።

በዚህም ተጠቃሚዎች የተላከላቸውን ሊንክ ሲጫኑ ወይም የተጠየቁትን መረጃ ሲሞሉ፣ የዋትሳፕ ወይም የቴሌግራም አካውንታቸው ወዲያውኑ በጠላፊዎች ቁጥጥር ስር እንዲዉል ያደርጋል።

ወንጀለኞቹ አንዴ የአንድን ሰው አካውንት ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ የተጠለፈውን አካውንት በመጠቀም በተጎጂው ስም ለቅርብ ወዳጅ ዘመዶቹና ለስራ ባልደረቦቹ “ድንገተኛ ችግር አጋጥሞኛል” የሚሉ የሀሰት የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄዎችን ይልካሉ።

ይህም ድርጊት በማህበረሰቡ መካከል ያለውን መተማመን ከመሸርሸሩ ባለፈ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በማጭበርበር እንዲመዘበር በማድረግ መጠነ-ሰፊ የኢኮኖሚና የስነ-ልቦና ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።

ከላይ የተጠቀሱና መሰል የሳይበር ደህንነት ስጋቶችን ለመቀነስ፣ የመንግስትና የግል ተቋማት እንዲሁም ማህበረሰቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ያሳስባል።

ከማይታወቁ ወይም ካልተረጋገጡ አድራሻዎች በዋትሳፕ፣ በቴሌግራም እና በሌሎች መድረኮች የሚላኩ ሊንኮችን ካለመክፈት ባለፈ፣ አጠራጣሪ መልዕክቶች ሲደርሱ ወዲያውኑ “Report” እና “Block” በማድረግ የጥቃቱን ስርጭት መግታት ይገባል።

በተጨማሪም ማንኛውንም አይነት ሚስጥራዊ የይለፍ ቃል ወይም በስልክ የሚላክ የማረጋገጫ ኮድ (Verification Code) ለማንም አካል አለመስጠት ለዲጂታል ደህንነታችን ወሳኝ መሆኑን አስተዳደሩ በድጋሚ ያስገነዝባል።

አስተዳደሩ እያንዳንዱ ተጠቃሚ በተለይም ማህበረሰቡ በመተግበሪያዎቹ ላይ የሁለትዮሽ ማረጋገጫ (Two-Step Verification) በአስቸኳይ እንዲተገብር ይመክራል።

ይህ የቴክኖሎጂ የመረጃ ጠላፊዎች የግለሰቦችን አካውንት በቀላሉ እንዳይቆጣጠሩ የሚያደርግ እና ተጨማሪ የደህንነት ቁልፍ የሚፈጥር አስተማማኝ የመከላከያ ዘዴ ነው።

ዜጎች ይህንን ቀላል ግን ውጤታማ የሆነ የደህንነት ጥንቃቄ ተግባራዊ በማድረግ፣ ራሳቸውን በቴክኖሎጂ ከታገዙ የማጭበርበር ድርጊቶች ሊታደጉና የሳይበር ወንጀለኞችን ሴራ ሊያከሽፉ እንደሚገባ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ይመክራል።

በመጨረሻም፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እነዚህን የሳይበር ወንጀለኞች በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ከሚመለከታቸው የጸጥታና የፍትህ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።

ማህበረሰቡ ማንኛውም የሳይበር ጥቃት ሙከራ ሲያጋጥመው ወይም አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎችን ሲመለከት በነጻ ስልክ መስመር 933 በመደወል ለኢመደአ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ እናቀርባለን።

የሳይበር ደህንነትን ማስጠበቅ የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን የሁላችንም የጋራ ሀላፊነት በመሆኑ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችንን በንቃትና በጥንቃቄ በመምራት የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት በጋራ እንጠብቅ።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ጥር 2018 ዓ.ም አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review