AMN – ጥር 20/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በአደገኛ ዕፅ ቁጥጥር የፖሊስን ስራ በከፍተኛ ደረጃ የሚያግዙ አነፍናፊ ውሾችን (K9) ከእስራኤል ፖሊስ በድጋፍ አግኝቷል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ ድጋፉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ በድጋፍ ያገኛናቸው K9 ኖች በቦሌ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት በኩል ከተለያዩ የውጪ ሀገራት ወደ ሀገራችን የሚገባውንና የሚወጣውን አደገኛ ዕፅ ለመከላከል እና ዝውውሩንም ባደገ ሁኔታ ለመቆጣጠር እንደሚያስችሉ ተናግረዋል።
አያይዘውም በK9 በመታገዝ ከውጪ ሀገር ወደ ሀገራችን የሚገባውንና የሚወጣውን አደገኛ ዕፅ በተገቢው መንገድ ለመቆጣጠር የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የፀረ-ፈንጂና የአደገኛ ዕፅ ቁጥጥር መምሪያ ባለሙያዎች በእስራኤል ሀገር ቴል አቪቭ ስልጠና እየወሰዱ መሆናቸውን ተናግረው፣ አነፍናፊ ውሾቹ ሰልጥነው ወደ ሀገራችን ሲገቡ ለ39ኛው አፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ አገልግሎት እንደሚሰጡ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከእስራኤል ፖሊስ ጋር በመተባበር አደገኛ ዕፅ ዝውውር በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ በእስራኤል ሀገር በቴል አቪቭ እየሰለጠኑ የሚገኙት K9ኖች ወደ ሀገራችን ገብተው ሥራ ሲጀምሩ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በቦሌ ኤርፖርት እየሰጠ ያለውን አገልግሎት እንደሚያዘምኑ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ጨምረው መናገራቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ ገልጿል።