AMN – ጥር 20/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ካለፈው ጥር 1 ጀምሮ እየተካሄደ ባለው የመንገድ ደህንነት ንቅናቄ መርሐ ግብር ባለፉት 3 ቀናት ብቻ በሶስት ክፍለ ከተሞች በተደረገ ቁጥጥር፣ 213 አሽከርካሪዎች ጠጥተው ሲያሽከረክሩ በመገኘታቸው በልዩ ደረጃ ጥፋት በገንዘብ መቀጣታቸው ተገለፀ ፡፡
የጥር ወር በሀገራችን በዓላት የሚበዙበት ወቅት እንደመሆኑ መጠን፣ በዚህ ወቅት ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት ስለሚኖር እና ከዚህ ጋር ተያይዞ ማህበረሰቡን ከትራፈክ አደጋ ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጥና የቁጥጥር ስራ በስፋት እየተሰራ መሆኑን የተቋሙ የህዝብ ግንኙነት እና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ወይዘሮ ገነት ዲባባ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ገልፀዋል፡፡
በመሆኑም የጥር ወርን የመንገድ ደህንነት ግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ ትምህርት ከመስጠት በተጓዳኝ፣ ለትራፊክ ግጭት ቀዳሚ መንስኤ በሆነው ጠጥቶ ማሽከርከር ላይ በተካሄደ የሶስት ቀናት ኦፕሬሽን በቦሌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት እስከ ለሊቱ 10፡00 1 ሺህ 376 አሽከርካሪዎች በአልኮል ትንፋሽ መርመሪያ መሳሪያ ተመርምረው 107ቱ ከልኬት በላይ ጠጥተው በመገኘታቸው በገንዘብ መቀጣታቸውን ወይዘሮ ገነት ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ከጉለሌ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከትራፊክ ፖሊስ አባላት ጋር በአዲሱ ገበያ አካባቢ ከምሽቱ 2፡00 እስከ ለሊቱ 6፡00 ባካሄደው ጥብቅ ቁጥጥር፣ 72 አሽከርካሪዎች ከልኬት በላይ ጠጥተው በማሽከርከራቸው የእርምት እርምጃ መወሰዱን ነው የገለጹት፡፡
በተመሳሳይ የየካ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከትራፊክ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት በወሰን መስመር ከምሽቱ 2፡00 እስከ ለሊቱ 6፡00 በተካሄደው ኦፕሬሽን፣ 675 አሽከርካሪዎች በትንፋሽ መመርመሪያ በሊትር ከ0.24 ሚሊግራም በላይ አልኮል የተጠቀሙ መሆናቸው በመረጋገጡ በገንዘብ መቀጣታቸውን ወይዘሮ ገነት አብራርተዋል ፡፡
ይኸው የመንገድ ደህንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ እና በደንብ ተላላፊዎች ላይ የሚካሄደው ቁጥጥር እስከ ጥር 30 ቀን 2018 የሚቀጥል መሆኑን ያነሱት ወይዘሮ ገነት፣ ማንኛውም አሽከርካሪ ከጠጣ ማሽከርከር እንደሌለበትና ይህንንም በማድረግ በትራፊክ አደጋ ከሚደርስ የማህበራዊ ቀውስ እና የኢኮኖሚ ኪሳራ ለመታደግ ሙያዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በያለው ጌታነህ