AMN – ጥር 20/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማን ተከትሎ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።
ከንቲባዋ በተለይ በኑሮ ውድነት፣ በተቋም ግንባታ እና በገቢ አሰባሰብ ዙሪያ በቀጣይ ወራት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የፖለቲካ ሥርዓት ቢቀያየር እንኳ መሰረታቸው የማይናወጥ ተቋማትን መገንባት አለብን ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ በየመሥሪያ ቤቱ ለውጥን የሚያመጡ ብቃት ያላቸው ሠራተኞችን ማፍራት ለአመራር ውጤታማነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ በበጀት ዓመቱ 18 ቢሊየን ብር ለድጎማ መመደቡን ያስታወሱት ከንቲባዋ፣ ይህ በጀት ለምገባ፣ ለተማሪዎች ዩኒፎርም፣ ለነዳጅ እና ለጤና መድኅን የሚውል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ ግማሽ የሚሆነውን በዚህ ስድስት ወር ውስጥ ለህዝብ ጥቅም አውለነዋል ሲሉም ከንቲባ አዳነች አቤቤ አክለዋል፡፡
ተረጂነትን መቀነስ እና የሥራ ዕድል መፍጠር የኑሮ ውድነት ቅነሳ ስትራቴጂ አካል መሆናቸውንም ነው የገለፁት፡፡
ሌብነትን ለመታገል የሕዝብ ጥቆማና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባዋ፣ የአካባቢ ልማት ሥራዎች በማኅበረሰቡ አደረጃጀት እንዲከናወኑ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ሆኖም ግን በማንኛውም መልኩ ባልታወቀ መንገድ ገንዘብ መሰብሰብ የተከለከለ መሆኑንና ሁሉም የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች በኦዲት ሥርዓት ሊያልፉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የገቢ አሰባሰቡ ከከተማዋ የማመንጨት ዓቅም ጋር ተመጣጣኝ አለመሆኑን ከንቲባዋ ገልፀው፣ የገቢ መዛባትን ለመቆጣጠር የወጡ አሠራሮች በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆኑ አሳስበዋል።
በበረከት ጌታቸው