AMN- ጥር 21/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ጎዳናዎችና ትምህርት ቤቶች ውስጥ በርካታ ታዳጊዎችን መመልከት የተለመደ ነው፣ አብዛኛዎቹ በዲጂታል ጨዋታዎችና በቪዲዮ ጌሞች ተጠምደው ሲታዩ፣ አሜን ባሳዝነው ግን የተለየ መንገድን መርጧል።
ገና በ10 ዓመቱ ከበርካታ አዋቂዎች በላይ መጻሕፍትን ገልጦ፣ የዕውቀት ባህር ውስጥ እየዋኘ የሚገኝ ታዳጊ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።
የአሜን ታሪክ የሚጀምረው እርሱ ወደዚህ ዓለም ከመምጣቱ በፊት ነው፣ እናቱ መምህርት እሴተ ታዬ፣ “ነፍሰ ጡር እያለሁ መጽሐፍትን አነብለት ነበር፤ይህም ሳይንሳዊና ሃይማኖታዊ መሰረት አለው” የምትለው እናቱ፣ በወቅቱ ብዙዎች ቢያፌዙባትም ዛሬ ግን ያየዘሩት ዘር ፍሬ አፍርቶ እያዩት ነው ይላሉ።
እናቱ እንደምትናገረው፣ ገና ሕፃን ሳለ ልክ እንደሚሰማቸው ሰው ሁልጊዜም ይነበብለት ነበር፣ ይህ ጥረት ዛሬ አሜንን ከ450 በላይ መጽሐፍት ማንበብ የቻለና ጥልቅ አሳቢ እንዲሆን አስችሎታ ትላለች።

አሜን ባሳዝነው በአሁኑ ወቅት በምስካዬ ኅዙናን መድሃኒዓለም ትምህርት ቤት የ5ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፣ የዕድሜ እኩዮቹ በስልኮቻቸው ‘ስፓይደር ማን’ ሲጫወቱ፣ እርሱ ግን “የሐበሻ ጀብዱ”ን እና የዶ/ር አለማየሁ ዋሴን ረቂቅ ስራዎች ያነባል።
ስለ ንባብ አስፈላጊነት ሲጠየቅ የሚሰጠው ምላሽ ከአንድ 10 ዓመት ታዳጊም የማይጠበቅ ግርማ አለው።
“የሰው ልጅ በተለያዩ መንገዶች እውቀት ሊያገኝ ይችላል፤ ግን ከቴክኖሎጂ በላይ እውቀትን ማግኘት የሚቻለው በመጽሐፍ ነው። በትምህርቴ ጎበዝ እንድሆን ብቻ ሳይሆን፣ ችግሮች ሲያጋጥሙኝ መፍትሄ እንድፈልግም አግዞኛል” ይላል።
በእነ አሜን ቤት ንባብ ግዴታ ሳይሆን የቤተሰብ ባህል ነው፤ “የቤተሰብ ንባብ” በሚለው ፕሮግራማቸው፣ ቤተሰቡ በአንድነት ተቀምጠው መጽሐፍትን በየተራ ያነባሉ። ይህ ልምድ በቤተሰቡ መካከል ያለውን ፍቅር ከማጥበቁም በላይ፣ አሜን የነገሮችን ጭብጥ በቀላሉ እንዲረዳም አድርጎታል።

ጎረቤቶቹ እና መምህራኑም አሜን ከእድሜ እኩዮቹ በተለየ ሁኔታ አስተዋይ፣ ረጋ ያለና የነገሮች መፍትሄ አፍላቂ እንደሆነም ጭምር ይመሰክራሉ። አሜን አሁን የአንባቢነት ደረጃውን አሻግሮ ወደ ጸሐፊነት ተሸጋግሯል።
“ተፅኖ ፈጣሪ ሰዎች ለኢትዮጵያ ልጆች” የተሰኘ መጽሐፍ እያዘጋጀ ሲሆን፣ መጽሐፉ በመጪው የካቲት 11 ቀን በልደቱ ዕለት ይመረቃል ተብሎ ይጠበቃል። ዓላማውም ልጆች የራሳቸውን ሀገር ጀግኖች እና ታላላቅ ሰዎች እንዲያውቁ ማድረግ ሲሆን፣ ልጆችን ‘አንብቡ’ የሚለውን ቃል ከመስማት ይልቅ፣ ቤተሰቦቻቸው ሲያነቡ ማየትን ይመርጣሉ፡፡
ስለዚህ ወላጆች በዚህ መንገድ ልጆቻቸውን መግራት ይችላሉ ሲሉ የአሜን እናት መምህርት እሰይ መልዕክታቸውን አጋርተዋል። የአሜን ታሪክ ለሁላችንም የሚያስተምረው፣ ንባብን ከልጅነት ጀምሮ በቤት ውስጥ ባህል ማድረግ ቢቻል፣ እንደ አሜን ያሉ ብሩህ ዓዕምሮ ያላቸውን ትውልዶች ማፍራት እንደሚቻል ነው።
በሚካኤል ህሩይ