በጥቁር አንበሳ የአየር ትርኢት ላይ ለተሳተፉና ድንቅ ብቃታቸውን ላሳዩ አብራሪዎች፣ የእውቅና ተሰጠ

You are currently viewing በጥቁር አንበሳ የአየር ትርኢት ላይ ለተሳተፉና ድንቅ ብቃታቸውን ላሳዩ አብራሪዎች፣ የእውቅና ተሰጠ

AMN ጥር 21/ 2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ “የአንበሶቹ ሰማይ – ኢትዮጵያ” በሚል ለቀረበውና የኢትዮጵያውያንን ልብ ላኮራው ደማቅ የአየር ትርኢት ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የእውቅናና የምስጋና መርሃ ግብር ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል “የነፃነትና የአንድነት ምልክት” በሚል መሪ ቃል በተከበረው በዚህ ታሪካዊ በዓል ላይ፣ የሀገሪቱን ሰማይ በጥበብና በጀግንነት ላደመቁት አብራሪዎች የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ተገኝተው የእውቅና ስጦታና ምስጋና አበርክተዋል።

ዋና አዛዡ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፣ አብራሪዎቹ በትርኢቱ ወቅት ያሳዩት የላቀ ብቃትና ጥበብ ከመደበኛው ወታደራዊ ተግባር ባሻገር የተቋሙን ዝግጁነትና የቴክኖሎጂ የበላይነት ለዓለም ያስመሰከረ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ አክለውም፣ “ከተቋማችን አልፎ ኢትዮጵያን አኩርታችኋል፤ የአየር ኃይልን የማድረግ አቅምም በተግባር አረጋግጣችኋል” በማለት የአብራሪዎቹን ጀግንነትና ታማኝነት አወድሰዋል።

ይህ ዕውቅና አብራሪዎቹ ለሀገር ሉዓላዊነትና የአየር የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚያደርጉትን ተጋድሎ የሚዘክር ከመሆኑም በላይ፣ ለተቋሙ ቀጣይ ትውልድ ትልቅ የሞራል መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑ መገለጹን የሃገር መከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለኤኤምኤን የላከዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review