AMN- ጥር 21/2018 ዓ.ም
በመዲናዋ በኮሪደር ልማት የተገነቡ መሰረተ ልማቶች ኢትዮጵያ ያላትን ባህል፣ወግ እና ትውፊት ለማስተዋወቅ ምቹ ዕድል መፍጠራቸውን የአዲስ አበባ ባህል እና ኪነ ጥበብ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አዲሱ ሻንቆ ገለጹ።
17ኛው ከተማ አቀፍ የባህል ፌስቲቫል በተለያዩ መርሃግብሮች ከጥር 23 እስከ 25 ለ3 ቀናት እንደሚካሄድ ተገልጿል።
“አዲስ አበባ የባህልና ፈጠራ ሞዛይክ” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው ይህ ፌስቲቫል ኢትዮጵያን የሚወክሉ ባህሎች እና ትውፊቶች የሚቀርበብት መሆኑም ተነግሯል።

ፌስቲቫሉ ባህልን ለማስተዋወቅ፣ አንድነትን ለማጠናከር እንዲሁም ባህላዊ የዕደ ጥበብ ውጤቶችን ለገበያ ለማቅረብ ያለመ መሆኑንም አቶ አዲሱ ገልፀዋል።
በፌስቲቫሉ የባህል አልባሳትን የሚያስተዋውቅ የፋሽን ማሳያ መርሐ ግብር የሚካሄድ ሲሆን የዕደ ጥበብ ውጤቶችም ይቀርብበታልም ተብሏል።
እየተቀየረ የመጣውን የስራ ባህልና የሰዓት አጠቃቀም የተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እንደሚኖር የገለፁት አቶ አዲሱ፣ በመዲናዋ በኮሪደር ልማት የተገነቡ መሰረተ ልማቶች ኢትዮጵያ ያላትን ባህል፣ ወግ እና ትውፊት ለማስተዋወቅ ምቹ ዕድል መፍጠራቸውንም ተናግረዋል።
በተጨማሪም የአመጋገብ ባህል ለመቀየር በሌማት ትሩፋት የመጡ ለውጦችም በዚህ የባህል ፌስቲቫል ላይ እንደሚቀርቡ ተገልጿል፡፡
በአሰግድ ኪዳነማሪያም