You are currently viewing

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በቀጠናው ዘላቂ ልማትን ከማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለዉ የልማት ተቋማት ገለጹ

AMN ጥር 21/2018 ዓ.ም

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና የገንዘብ ሚኒስትሮች እና የልማት አጋሮች ከፍተኛ ተወካዮች በተሳተፉበትና በሞቃዲሾ በተካሄደው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል።

ዉይይቱ የቀድሞ ምክክሮችን መሰረት በማድረግ፣ የኢነርጂ አቅርቦት ፋይናንስን እና ቀጠናዊ ትስስርን ለማፋጠን በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ ነዉ፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ለቀጠናው የጋራ እድገትና መረጋጋት የኢነርጂ ትስስር ያለውን ወሳኝ ጠቀሜታ በማስረዳት፣ ለዚህም ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይ ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ማመንጫዎችን በማስፋፋት እና በቀጠናዊ የኃይል ትስስር ረገድ እያሳየች ያለውን እድገት አቶ አህመድ ሽዴ በዉይይቱ ወቅት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ከሱዳን፣ ጅቡቲ እና ኬንያ ጋር ካላት የኃይል መስመር ትስስር በተጨማሪ፣ የልማት አጋሮች ከሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ጋር ለሚደረጉ አዳዲስ የኃይል ትስስሮች የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ያላቸዉን ፍላጎት አሳይተዋል።

በመድረኩ ላይ የዓለም ባንክ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንቶች፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ፣ የኮመንዌልዝ እና የልማት ቢሮ (FCDO) እንዲሁም የጀርመን የልማት ሚኒስቴር ተወካዮች ተገኝተዋል። አጋሮቹ እንደ “ሚሽን 300” ባሉ ተነሳሽነቶች አማካኝነት የኃይል አቅርቦትን ለማስፋፋት ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

ተሳታፊዎቹ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በቀጠናው ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ያለውን ከፍተኛ አቅም እውቅና ሰጥተዋል።

ሚኒስትሮቹ የፖሊሲ መጣጣምን ለመከታተል እና የኢነርጂ ትስስሩን ለማፋጠን የሚሰራ ከፍተኛ የኮሚቴ አባላት እንዲቋቋሙ ተስማምተዋል።

ከሚኒስትሮች ስብሰባው በኋላ፣ አቶ አህመድ ሽዴ ከሶማሊያ ፕሬዝዳንት ጋር ተገናኝተው መወያየታቸዉን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review