AMN- ጥር 21/2018 ዓ.ም
ዘመኑ ያመጣውን ዕድል በመጠቀም በኢንዱስትሪው ዘርፍ አዲስ የስራ ባህል መገንባት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራና ክህሎት ቢሮ ገለፀ።
ቢሮው ምክክር ለምርታማነት ንቅናቄ እና የማህበራት የመደራጀት ምጣኔ ማሳደግን ያለመ ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል።
በውይይት መድረኩ ላይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ፣ ዘመኑ ያመጣውን ዕድል በመጠቀም በኢንዱስትሪ ዘርፍ አዲስ የኢንዱስትሪ ባህል መገንባት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪው ዘርፍ የዕድገትታችን መሰረት በመሆኑ በልዩ ትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በኢንዱስትሪው ዘርፍ የመደራጀት ምጣኔ እንዲያድግ ተናቦና ተቀራርቦ በጋራ መስራትን ይጠይቃል ብለዋል።
ምርታማነት ለማሳደግ እና ከስራ ባህል ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ መንግስት፣ አሰሪ እና ሰራተኛው ኃላፊነታቸውን መውጣት እንደሚጠበቅባቸው በውይይት መድረኩ ተነስቷል።
በአሰሪና ሰራተኛ መካከል ሰላማዊ ግንኙነት እንዲሰፍን ምክክር ወሳኝ እንደሆነም ተጠቅሷል።
ሀገር ወዳድ የኢንዱስትሪ ማህብረሰብ ለመገንባት በጋራ መስራት እንደሚገባም ተገልጿል።
የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የሰራተኞች ማህበራት እና የአሰሪ ማህበራት አመራሮች በውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች ናቸው።
በዳንኤል መላኩ