በአዲስ አበባ ከተማ የተሰጠው የመጀመሪያ ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በስኬት ተጠናቀቀ

You are currently viewing በአዲስ አበባ ከተማ የተሰጠው የመጀመሪያ ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በስኬት ተጠናቀቀ
  • Post category:ጤና

AMN- ጥር 21/2018 ዓ.ም

‎በአዲስ አበባ ከተማ የተሰጠው የመጀመሪያ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ስኬታማ እንደነበር የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ገለጸ።

‎ቢሮው በመጀመሪያ ዙር በተሰጠው የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ አፈጻጸም ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ ግምገማ እያካሄደ ነው።

‎እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ፖሊዮ ዘላቂ የአካል ጉዳትንና ሞትን የሚያመጣ በሽታ ነው። ለበሽታው ምንም አይነት መድኃኒት ስላልተገኘለት በሽታውን መከላከል የሚቻለው በክትባት ብቻ ነው፡፡

‎በቫይረሱ የተጠቃ አንድ ህፃን ከ200 በላይ ሌሎች ሕፃናትን ለበሽታው ሊያጋልጥ ይችላል። ይህንን ለመከላከልም በሀገር አቀፍ ደረጃ በየጊዜው በዘመቻ መልኩ ክትባት እየተሰጠ ቀጥሏል።

‎የዚህ ዓመት የክትባት ዘመቻም ከታህሳስ 3 እስከ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ባሉት 4 ቀናት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተሰጠ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማም ክትባቱ ለሚያስፈልጋቸው ከ5 ዓመት በታች ላሉ ሕፃናት ሙሉ ለሙሉ በመስጠት በስኬት መጠናቀቁን የከተማዋ ጤና ቢሮ ገልጿል።

ከ7 መቶ ሺህ በላይ ሕጻናትን ለመከተብ 869 ከታቢ ቡድን እና በቡድኑ ውስጥ 4ሺ 028 ባለሙያዎችን በመመደብ ወደ ስራ የገባው ቢሮው፣ ከዕቅድ በላይ ከ8 መቶ ሺህ በላይ ህፃናትን መከተቡን የቢሮው ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አለማየሁ ወንድሙ ተናግረዋል፡፡

‎ለክትባቱ ስኬት የባለድርሻ አካላት ሚና የላቀ መሆኑን የገለጹት አቶ አለማየሁ በተለይ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክና የከተማው ትምህርት ቢሮ አበርክቷቸው ከፍተኛ እንደነበርም አንስተዋል።

‎አቶ አለማየሁ አክለውም ግምገማው ያጋጠሙ ክፍተቶችን በመለየት በቀጣይ ዙር ለሚደረገው የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ግብዓት የሚሆኑ አሰራሮችን ለማግኘት ያስችላል ብለዋል።

በሔለን ጀንበሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review