AMN – ጥር 22/2018 ዓ.ም
በህጻናት ላይ የሚከሰት የቶንሲል ኢንፌክሽን በአግባቡና በወቅቱ ካልታከመ ለከፋ የልብ ህመም መንስኤ ሊሆን እንደሚችል በየካቲት 12 ሜዲካል ኮሌጅ የህፃናት ህክምና ስፔሻሊስት ሀኪም ዶ/ር መቅደስ ሽመክት ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
ዶ/ር መቅደስ እንደገለጹት፤ በአብዛኛው በህፃናት ላይ የሚከሰተው የልብ ህመም የቶንሲል ባክቴሪያን ለመከላከል የሚመረተው የሰውነት መከላከያ (Antibody) የልብ ቫልቮችን በሚያጠቃበት ወቅት ነው።

አንድ ህጻን ከቶንሲል ኢንፌክሽን ካገገመ ከሁለት እስከ አራት ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥ ልዩ ትኩረት የሚሹ ምልክቶች ሊታዩ እንደሚችሉ ዶክተሯ ገልጸዋል።
በመገጣጠሚያዎች ላይ የሚከሰት ከፍተኛ ህመም እና እብጠት የልብ ህመም ዋነኛው ምልክት መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር መቅደስ፤ ህመሙ በአብዛኛው ከጉልበት ወደ ቁርጭምጭሚት ወይም ወደ ክርን የመዘዋወር ባህሪ እንዳለውም አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ህጻኑ በቂ እረፍት በሚያደርግበት ወቅት እንኳን የልብ ምቱ መጨመር፣ የትንፋሽ ማጠር እና ከመጠን ያለፈ ድካም ማሳየት በቶንሲል ምክንያት ለሚከሰት የልብ ህመም ምልክቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
አልፎ አልፎ ህጻናት እጅና እግራቸውን በራሳቸው ፍቃድ መቆጣጠር የማይችሉበት አጋጣሚ ሊፈጠር እንደሚችል ባለሙያዋ አክለዋል።

የልብ ህመምን ለመከላከል ወላጆች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ዶ/ር መቅደስ ይመክራሉ። ህጻናት የቶንሲል ህመም ምልክት ሲያሳዩ በአስቸኳይ ወደ ህክምና ተቋም በመውሰድ ትክክለኛውን ምርመራ እንዲያገኙ ማድረግ ቀዳሚው ተግባር መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።
ዶ/ር መቅደስ አክለውም ለቶንሲል ኢንፌክሽን የታዘዙ የፀረ-ባክቴሪያ መድኃኒቶችን የህጻኑ ጤንነት መሻሻል ቢያሳይም እንኳን ሳይቆርጡ እስከ መጨረሻው ማጠናቀቅ እንደሚገባ ገልጸው፤ መድኃኒቱን አቋርጦ መተው ባክቴሪያው በሰውነት ውስጥ እንዲቆይና በኋላ ላይ ልብን እንዲያጠቃ እድል እንደሚሰጠውም ተናግረዋል።
በመሆኑም የልጆችን የልብ ጤንነት ለመጠበቅ የቶንሲል ህመም በቸልታ አለመመልከትና የህክምና ክትትልን ማጠናከር እንደሚገባ ዶ/ር መቅደስ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ አስገንዝበዋል፡፡
በበረከት ጌታቸው