AMN ጥር 21 ቀን 2018 ዓ.ም
የዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ ከሰጣቸው የጎዳና ላይ ውድድሮች አንዱ የሆነው የዱባይ ማራቶን በመጪው እሁድ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዱባይ ይደረጋል፡፡
25ኛውን የዱባይ ማራቶን ለሚያሸንፉ አትሌቶች የአንድ መቶ ሺ ዶላር ሽልማት ተዘጋጅቷል፡፡ የዓለም ፈጣን ሰዓትን ለሚያስመዘግቡ አትሌቶች ደግሞ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ሽልማት እንደተዘጋጀ ይፋ ተደርጓል፡፡
የዱባይ ማራቶን የመሮጫ መስመሩ ለጥ ያለ በመሆኑ ፈጣን ሰዓት ከሚመዘገብባቸው ማራቶች አንዱ ነው፡፡
መጨረሻውን ዱባይ ፖሊስ አካዳሚ የሚያደርገው የዘንድሮ ውድድር የሚጠበቁ አትሌቶችን አትሌቲክስ ዊክሊ ይፋ አድርጓል፡፡
በወንዶች ጋዲሳ ብርሃኑ እና ብርሃኑ ጸጉ እንዲሁም በሴቶች ፋንቱ ወርቁ እና አንቺናሉ ደሴ በኢትዮጵያ በኩል የሚጠበቁ አትሌቶች መሆናቸውን ዘገባው ጠቅሷል፡፡
የ33 ዓመቱ ጋዲሳ 2025ን በስኬት አሳልፏል፡፡ ጋዲሳ ከሦስት ወራት በፊት የተካሄደውን ሊዝበን ማራቶን በሁለተኛት ሲያጠናቅቅ የገባበት 2:07:25 ሰዓት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ እንዲሁም ፕራግ ማራቶንን በ8ኛነት አጠናቆ ነው ዱባይ የደረሰው፡፡

ጋዲሳ የ2023ቱን የሲቪያ ማራቶን በበላይነት ሲያጠናቅቅ የገባበት 2:04:59 የራሱ የምንጊዜም ምርጥ ሰዓቱ ነው፡፡ ጋዲሳ የታይፒ ማራንቶንም አሸናፊ ነው፡፡ የኮፐንሃገን ማራቶንን በሁለተኛነት ማጠናቀቁም የሚታወስ ነው፡፡
ብርሃኑ ጸጉም ቀላል ግምት አልተሰጠውም፡፡ የባለፈው ዓመቱን የዱባይ ማራቶን ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ የገባበት 2:05:14 የራሱ ምርጥ ሰዓት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ የ2019ኙ አፍሪካ ጨዋታዎች የ10 ሺ ሜትር አሸናፊው ብርሃኑ ፣ ከኮፐንሃገን ግማሽ ማራቶን ጋር በተገናኘ በአበረታች መድሃኒት ተጠቃሚነት ታግዶ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡ አበራ ኩማ ፣ ደርቤ ሮቢና አይቼው ባንቴ ሌሎች እሁድ የሚጠበቁ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው፡፡
2:05:47 ፈጣን ሰዓት ያለው ኬንያዊው ኤሪክ ኪፕሮኖ ሌላው የሚጠበቅ አትሌት ነው፡፡ የ2020ውን ዱባይ ማራቶንን በሁለተኛነት ያጠናቀቀው ኪፕሮኖ የበርሊን ግማሽ ማራቶን ሪከርድ ባለቤት መሆኑ ይታወቃል፡፡
የሴቶቹን ፋንቱ ወርቁ ለማሸነፍ ቀዳሚውን ግምት ወስዳለች፡፡ ከ1500 ሜትር ሩጫን የጀመረችው ፋንቱ በ2025ቱ የበርሊን ማራቶንን ያስመዘገበችው 2:21:57 ተስፋ ሰጪ ሰዓቷ ነው፡፡
የባለፈው ዓመት የሲቪያ ማራቶን እና ቤጂንግ ማራቶን አሸናፊዋ አንቺናሉ ደሴ ሌላዋ የምትጠበቅ አትሌት ናት፡፡ በ2023ቱ የዱባይ ማራቶንን የገባችበት 2:23:17 የራሷ ምርጥ ሰዓት የሆነላት ትግስት ጌትነት ሌላዋ ተጠባቂ አትሌት ናት፡፡
የ2012ቱ ለንደን ማራን የሶስት ሺ ሜትር መሰናክል ሜዳሊስቷ ሶፊያ አሰፋ ሌላኛው የዱባይ ማራቶን ተጠባቂ አትሌት ናት፡፡ አትሌት አበበች አፈወርቅም ቀላል ግምትል አልተሰጣትም፡፡
የዱባይ ማራቶን የምንጊዜውም ፈጣን ሰዓትን በወንዶች ጌታነህ ሞላ በሴቶች ትዕግስት ከተማ እንደያዙት የሚታወቅ ነው፡፡
በታምራት አበራ