AMN- ጥር 22/2018 ዓ.ም
የሀገሬ መዲና እና የአዲሱ ሬስቶራንቴ “ማርከስ አዲስ” መገኛ የሆነችው አዲስ አበባ፤ የኢትዮጵያ እምብርት ብቻ ሳትሆን የባህላችንም መገለጫ ናት ሲል ይጀምራል እውቁ ዓለም አቀፍ የምግብ ባለሙያ /ሼፍ/ ማርቆስ ሳሙኤልሰን ስለ አዲስ አበባ ሲናገር።
“ኢተር ዶት ኮም” ከተሰኘው ድረ-ገፅ ጋር ቆይታ ያደረገው ማርቆስ ሳሙኤልሰን፣ በአዲስ አበባ የኪነ-ጥበብ ተቋማት እና የምግብ አዳራሾች የማይነጣጠሉ የተጣመሩ ናቸው ሲል ይገልፃል።
የስዕል ማሳያዎች (ጋለሪዎች)፣ ሙዚየሞች እና ገበያዎች ተቀናጅተው በከተማዋ ሬስቶራንቶች እና ማብሰያ ቤቶች ውስጥ ልዩና አስደማሚ ስሜት ይፈጥራሉ። የኢትዮጵያ ምግብ መገለጫ በሆነው “በርበሬ” ውስጥ የከተማዋን ትርታ ማጣጣም ይቻላል።

“በርበሬ” በአዲስ አበባ መኖሪያ ቤቶችና ምግብ ቤቶች ውስጥ የማይታጣ የጣዕም ሚስጥር ሲሆን፣ በበዓላት ወቅት በእንቁላል ታጅቦ በሚቀርበው ዝነኛው ምግብ “ዶሮ ወጥ” ውስጥ ወሳኝ ግብዓት ነው፡፡ አዲስ አበባ በለውጥ ላይ ናት! በወጣቱ ቁጥር ብዛት የተነሳ በየቦታው ንቁ እንቅስቃሴና ግንባታዎች ይታያሉ።
ጥንታዊው ሰብላችን “ጤፍ” ዛሬ ወደ ቴላቴሊ ፓስታ ተቀይሮ ቀርቧል፤ ዝነኛው “ክትፎ” ደግሞ በአዳዲስ የቅመም አይነቶች ተከሽኖ ዘምኗል። ዛሬ በአዲስ አበባ በባህላዊ ምግቦች፣ በጎዳና ምግቦች (ፈጣን ምግቦች) እና በዘመናዊ የምግብ አሰራሮች መካከል ሰፊ ምርጫ አለ።
በአዲስ አበባ መጎብኘት አለባቸው ያላቸውን ቦታዎች የጠቆመው ዝነኛው የምግብ ባለሙያ ማርቆስ፣ ቃተኛን (Kategna) ሳያዩ አይሂዱ ይላል፡፡
ቃተኛ (Kategna) ወደ አዲስ አበባ መጥተው ሳይረግጡት የማይታለፍ ቦታ ነው በማለት፣ ባህላዊ ምግቦች፣ ውዝዋዜ እና ሙዚቃ በአንድ ላይ የሚቀርቡበት እውነተኛ የባህል ማዕከል እንደሆነም ይገልፃል። ሌላኛው የጠቀሰው ቦታ ትራቶሪያ ጉስቶ (Trattoria Gusto) ሲሆን፣ የኢትዮጵያ እና የጣሊያን ጣዕም የሚዋሃድበት ዘመናዊ ሬስቶራንት መሆኑን ያነሳል።

በሀገር ውስጥና በውጭ ተምረው የመጡ ወጣት ሼፎች በጤፍ አዳዲስ የምግብ አይነቶችን የሚፈጥሩበት ቦታ እንደሆነም አመልክቷል። ሌላው የጠቀሰው ሥፍራ የከተማዋ የልብ ትርታ የሆነውን መርካቶን ሲሆን፣ የአፍሪካ ግዙፉ የውጭ ገበያ “መርካቶ” በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚኖሩበት እና የሚነግዱበት ልዩ ዓለም መሆኑን አንስቷል።
ቅመማ ቅመም፣ ቡና፣ በርበሬ፣ ምስር የመሳሰሉ ግብዓቶችን በባህላዊ መንገድ ተቆልለው ሲመዘኑ ማየትና ከዛም መከራከር እጅግ አስደሳች ሁነት ስለመሆኑም ይናገራል። መርካቶ በየዘርፉ የተከፋፈለ ሲሆን፣ የእንስሳት ተራ፣ የቅመም ተራ እና የጨርቃጨርቅ ተራ ተለይተው የተደራጁ መሆናቸውን ያነሳል።
አዲስ አበባ አሮጌውና አዲሱ ዓለም የሚገናኙባት፣ በምግብ፣ በፖድካስት፣ በኪነ-ጥበብ እና በሙዚቃ የደመቀች ከተማ ናት ይላል። የኢትዮጵያ መዲና ገና ጉዞዋን እየጀመረች እንደሆነም ይሰማኛል! ሲልም ያጠቃልላል፡፡
በታምራት ቢሻው