• በአዲስ አበባ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት 2 ሺህ 556 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል
አቶ ታደለ ታፈሰ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ነዋሪ ናቸው፡፡ እየገነቡት ለሚገኘው ባለሰባት ወለል ሁለገብ ህንጻ (G+7) ማጠናቀቂያ የሚሆኑ የበር፣ መስኮትና የተለያዩ እቃዎችን ለማስገባት የኢንቨስትመንት ፈቃድ አውጥተዋል፡፡ ፈቃዱን በውክልና ያወጡለት በአሜሪካ ሀገር እየኖሩ ላሉት ትውልደ ኢትዮጵያዊ የህክምና ባለሙያ ዶ/ር መስፍን አለማየሁ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
አቶ ታደለ የኢንቨስትመንት ፈቃዱን ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መሄድ ሳያስፈልጋቸው አስፈላጊውን መረጃ በማሟላት በኦንላይን በአጭር ጊዜ ማግኘታቸውንaa ይናገራሉ፡፡ “ያገኘሁት አገልግሎት አመርቂ ነው፡፡ ቀደም ሲል ረጅምና ውስብስብ የነበረው አገልግሎት በጣም ቀላል ሆኗል፡፡ የሲስተም አጠቃቀሙ ግልፅ ነው” ሲሉ ባገኙት አገልግሎት መርካታቸውን ተናግረዋል። ቀደም ሲል ፋይል ወጥቶ፣ ወረፋ ተይዞ፣ ከአንድ ቢሮ ሌላ ቦታ ተመላልሶ ይገኝ የነበረው አገልግሎት ቤት ድረስ እንደመጣና በዚህም ደስተኛ እንደሆኑ አክለዋል፡፡
ሌላኛው አስተያየታቸውን ያጋሩን አቶ ኪሩቤል አለማየሁ ይባላሉ። ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ፕላስቲክን የሚተኩ ቦርሳዎችን በማምረት መሰማራት ይችሉ ዘንድ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለማውጣት ወደ ኮሚሽኑ መጥተው ነበር ያገኘናቸው፡፡ አገልግሎቱ በኦንላይን የሚሰጥ ቢሆንም ሲስተሙ ቶሎ ምላሽ ሊሰጣቸው ስላልቻለና በቶሎ ፈቃዱን ማውጣት ስላለባቸው ወደ ኮሚሽኑ በአካል መምጣታቸውን ነግረውናል። “ሲስተሙ ፈጣን አይደለም፤ ጊዜ ይወስዳል፤ እየሄደ እያለ በመሃል ይቆማል፤ በቶሎ ምላሽ አይሰጥም፡፡” በማለት መፈተሽ እንዳለበት አንስተዋል፡፡ ለ15 ዓመታት ያህል በስደት ደቡብ አፍሪካ መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ለኢንቨስተሮች የሚሰጠውን አገልግሎት ለማቃለል ከዚህም በላይ መሰራት እንዳለበት አክለው ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው ያለውን የኮንስትራክሽን ማሽነሪ ኪራይ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመመለስ መምጣቱን የነገረን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ነዋሪ ወጣት ተመስገን አበበ ይባላል፡፡ “በኮሚሽኑ የሚሰጠው አገልግሎት በጣም ጥሩ ነው፡፡ ከአገልግሎት ሰጪዎች ጋር በአካል የምንገናኝበት ብዙ እድል የለም፡፡ በኦንላይን ነው የሚሰጠው፡፡ ፋይሎችን ለማየትና ለአንዳንድ ጥያቄዎች ካልሆነ በስተቀር በአካል መምጣት አያስፈልገንም፡፡ ቤት ሆነን አገልግሎት እያገኘን ነው፡፡ ይህ ደግሞ በመመላለስ እናጠፋ የነበረውን ጊዜና ገንዘብ ቆጥቦልናል” ሲል በአገልግሎቱ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡
አቶ ተክልዬ አካሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢንቨስትመንት ኮሚሽን የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በአንድ ማዕከል ውስጥ አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ፣ የማስፋፊያ ፈቃድ፣ የኢንቨስትመንት እድሳት፣ ምትክ፣ ለውጥ፣ ስረዛና መሰል የኢንቨስትመንት አገልግሎቶች ይሰጣሉ። ከዚህ ቀደም እነዚህ አገልግሎቶችን ተገልጋዮች በአካል መጥተው ፎርም በመሙላት ሲያገኙ እንደነበር ያነሳሉ፡፡
በማንዋል ሲሰጥ በነበረው አገልግሎት ተገልጋዮች የሚጠበቅባቸውን መስፈርት አሟልተው እስከመጡ ድረስ የተሻለ የሚባል አገልግሎት ሲያገኙ እንደነበር የገለፁት አቶ ተክልዬ፤ ተገልጋዮች ባገኙት አገልግሎት ያላቸውን አስተያየት በየጊዜው እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡ ብዙዎችም በሚሰጣቸው አገልግሎት ደስተኛና እርካታ እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡
የጋዜጣዋ ዝግጅት ክፍል የተመለከተው ከተገልጋዮች አስተያየት የተሰበሰበበት ቅፅ መረጃ የሚያሳየው በአገልግሎቱ ደስተኛ መሆናቸውን ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ተገልጋዮች ባሉበት ቦታ ሆነው በአካል መገኘት ሳያስፈልጋቸው በኦንላይን ማመልከቻ ወይም ፎርም ላይ አስፈላጊ መረጃዎችን አሟልተው በመሙላት አገልግሎት እያገኙ ይገኛሉ። አገልግሎት ፈላጊው የሚጠየቀውን መረጃ በኦንላይን ሲጭን ወዲያው ሰነዶች ታይተው አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ በዚህም ተገልጋዩ ወደ ቢሮ በመምጣት ሲያባክን የነበረውን ጊዜና ገንዘብ መቆጠብ ማስቻሉን አቶ ተክልዬ ጠቁመዋል፡፡
ዳይሬክተሩ በማብራሪያቸው፣ በአንድ ማዕከል የሚሰጡ የኢንቨስትመንት አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ አስደግፎ መስጠት የተጀመረው በ2017 ዓ.ም ከጥር ወር ጀምሮ ነው፡፡ ባለፈው አንድ ዓመትም የኦንላይን አገልግሎት አሰጣጡ እየታየ፣ ችግሮች ሲፈጠሩ ማስተካከያ ሲደረግ ቆይቶ ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ በይፋ ወደ ሙሉ ትግበራ ተገብቷል፡፡ ባለሙያውም ሆነ ተገልጋዩ (ባለሀብት) አገልግሎቱን በአግባቡ በመረዳት እየተጠቀመበት ነው። አገልግሎቱ ከፋይዳ መታወቂያ ጋር ተሳስሮ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም በኮሚሽኑ በአንድ ማዕከል የሚሰጡ አገልግሎቶች በአዲስ መሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል የመንግስት አገልግሎትም እየተሰጡ እንደሚገኙ ያስረዳሉ፡፡
የኢንቨስትመንት ፈቃድና መሰል አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ ተደግፈው መሰጠታቸው አገልግሎቱን ፈጣንና ቀልጣፋ በማድረግ ለባለሀብቱና ለከተማዋ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ትርጉም እንዳለው አቶ ተክልዬ ይናገራሉ። አንድ ባለሀብት ኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት አስቀድሞ ፈቃድ ማውጣት ይኖርበታል፡፡ ፈቃድ ያገኘ ባለሀብት ከባንክ ብድር ማግኘትን፣ የካፒታል እቃዎች ከውጭ ማስገባትን፣ የመስሪያ ቦታ ማግኘትን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ለማግኘት ይጠቅመዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ሳይንገላታ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ማግኘት የሚችል ከሆነ ሌሎች ድጋፎችን ለመጠየቅና ለማግኘት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርለት ገልጸዋል፡፡
ከአንድ ተገልጋይ የሲስተም መቆራረጥ ችግር እንዳለ የተነሳውን ሀሳብ በተመለከተ አቶ ተክልዬ ሲመልሱ፤ የሲስተም መቆራረጥ ችግር እንደሚያጋጥም አምነው፤ ችግሩ ሲያጋጥም ለተቋሙ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎችና ለተቋሙ ኮሚሽነር እንዲያውቁት በማድረግ መፍትሔ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል፡፡
በከተማዋ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወር ውስጥ 1 ሺህ 750 አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ 2 ሺህ 556 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል። የማስፋፊያ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ደግሞ ለ140 ባለሀብቶች ለመስጠት ታቅዶ 167 ባለሀብቶች ተሰጥቷል፡፡ የማሻሻያ ፈቃድ ለ202፣ የኢንቨስትመንት እድሳት ለ987 ባለሀብቶች እና የስረዛ አገልግሎት ለማግኘት የሚመጡትን በሙሉ አገልግሎቱን እንዲያገኙ ማድረግ በሚል የተያዘውን ዕቅድም ማሳካት ተችሏል፡፡
ሌላው በኮሚሽኑ በርካታ ተገልጋዮች የሚስተናገዱበትና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት የሚሰጥበት የክትትልና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ነው፡፡ አቶ ብሩክ እስተዚያ በኮሚሽኑ የፕሮጀክቶች ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክተር ናቸው። በዚህ ክፍልም በአገልግሎት ዘርፍ ማለትም በኮንስትራክሽን፣ ሆቴል፣ ጤና፣ ትምህርት፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ፕሮጀክቶች ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል፡፡ ድጋፎቹ እንደየፕሮጀክቶቹ ባህርይ የተለያየ ዓይነት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶች በኮሚሽኑ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የሚሰጠው ከደረጃ አምስት እስከ ደረጃ አንድ ላሉት ነው፡፡
በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ተቋራጮች በደረጃቸውና ደረጃቸውን ሲያሽሽሉ የሚያስፈልጋቸውን ማሽነሪዎች ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡና ቀረጥ ከፍለው ለፕሮጀክቶቻቸው አስፈላጊ የሆኑ ማሽኖችን እንዲያስገቡ ድጋፍ ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ ገልባጭ መኪና፣ ዶዘር፣ ክሬን፣ ኤክስካቫተር የመሳሰሉ ማሽኖችን የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው ደንብ መሰረት ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ የድጋፍ ደብዳቤ ይጻፍላቸዋል፡፡ መሬት እና የግንባታ ፈቃድ ላገኙ፣ በቱሪዝም ሚኒስቴር በኮከብ ደረጃ አገልግሎት እንደሚሰጡ ማረጋገጫ ላላቸው፣ ከኮሚሽኑ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ላወጡ ሆቴሎችም ድጋፍ ይደረጋል፡፡ ድጋፉ ለኢንቨስትመንቱ የሚያስፈልጋቸውን የግንባታ እቃዎች ከውጭ ከቀረጥ ነፃ ገዝተው እንዲያመጡ ለገንዘብ ሚኒስቴር ደብዳቤ ይፃፋል። የካፒታልና መገልገያ ዕቃዎችንም እንዲያገኙ የድጋፍ ደብዳቤ ይፃፋል፡፡ ልክ እንደሆቴሎች ሁሉ በትምህርት፣ ጤና እና ሌሎችም ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶች የሚያስፈልጋቸውን እቃ ከቀረጥ ነፃ ማስገባት እንዲችሉ የድጋፍ ደብዳቤ እንደሚፃፍላቸው አብራርተዋል፡፡
በፕሮጀክቶች ክትትልና ድጋፍ ዘርፍ ከሚሰጡ አገልግሎቶች የፋሲሊቴሽን አገልግሎት ሌላኛው ሲሆን ባለሀብቶች የብድር አገልግሎት የሚፈልጉ ከሆነ ለባንክ የድጋፍ ደብዳቤ፣ የመሰረተ ልማት ችግር (መብራት፣ ውሃና ሌሎች) ከሆነ መሰረተ ልማት ለሚያቀርቡ ተቋማት ትብብር እንዲደረግላቸው የድጋፍ ደብዳቤ ይፃፋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የገቢ ግብር እፎይታ ለሚያሰጣቸው ፕሮጀክቶች ኮሚሽኑ የሚገባቸው መሆኑን በማየት እንዲሰጣቸው ለሚመለከታቸው አካላት የድጋፍ ደብዳቤ ይፅፋል፡፡
ከዚህ ቀደም ባለሀብቱ እነዚህን አገልግሎቶች ለማግኘት በአካል መምጣት ይጠበቅበት ነበር፡፡ ከባለፈው ታህሳስ ወር 2018 ዓ.ም ጀምሮ ሁሉም የድጋፍና ክትትል አገልግሎት በቴክኖሎጂ ተደግፎ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ባለሀብቶች ባሉበት ሆነው ጥያቄዎችን በኦንላይን የሚያቀርቡ ሲሆን እንደየአግባብነቱ እየታየ በኦንላይ መልስ ይሰጣቸዋል፡፡ በዚህም ወደ ቢሮ በመመላለስ የሚያባክኑትን ጊዜና ገንዘብ በስራቸው ላይ እንዲያሳልፉ አግዟቸዋል።
ከዚህ ቀደም ፋይል ከመዝገብ ቤት ተፈልጎ በማውጣት ከባለሙያ ወደ ዳይሬክተርና ኮሚሽነር እየሄደ ነበር የሚሰራው፡፡ አሁን ላይ ፋይሎች ተደራጅተው በኦንላይን ስለገቡ፣ ከባለሙያ እስከ ኮሚሽነር ያሉት በቀላሉ በኦንላይን የተሰራውን ስራ በማየት አገልግሎት መስጠት የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በዚህም የፋይል ምልልስን በማስቀረት አገልግሎቱን ፈጣንና ቀልጣፋ ከማድረግ ባሻገር የስራ ጥራትን ማሳደግ እንዳስቻለ አቶ ብሩክ አብራርተዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር ባለሙያው መስክ በመሄድ በታብሌት መረጃውን የሚያስገባበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት በመስክ በመሄድ ፕሮጀክቶች ወደ ስራ እንዲገቡ ድጋፍ ከማድረግ አኳያ 470 ፕሮጀክቶች ላይ ክትትልና ድጋፍ ለማድረግ ታቅዶ 425ቱ ላይ ተደርጓል። በአገልግሎት ዘርፍ በስድስት ወራት ውስጥ 120 ፕሮጀክቶች ስራ እንዲጀምሩ ድጋፍ ለማድረግ ታቅዶ 124 ፕሮጀክቶች ስራ ለመጀመር ወደ እንቅስቃሴ (የካፒታል እቃ ወደ መግዛት) ገብተዋል፡፡ በዘርፉ 59 ፕሮጀክቶች ወደ ምርትና አገልግሎት መስጠት እንዲሸጋገሩ ለመደገፍ ታቅዶ 57ቱ ወደ ስራ ገብተዋል። ወደ ስራ የገቡት ፕሮጀክቶች ወደ 9 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ገንዘብ እያንቀሳቀሱ መሆኑን አቶ ብሩክ ጠቅሰዋል፡፡
ለባለሀብቶች በሚደረገው ድጋፍ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ጉምሩክ ኮሚሽን፣ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ ባንኮችን ጨምሮ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመቀናጀት እየሰሩ እንደሚገኙ አቶ ብሩክ ጠቁመዋል፡፡ ተገልጋዮች ባሉበት ሆነው addisinvest.gov.et ላይ በመግባት ማንኛውም ጥያቄ በማቅረብ አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ አክለው ጠቁመዋል፡፡
በቴክኖሎጂ የተደገፈው አገልግሎት ሲፈተሽ
አቶ ክንደንጉስ ገረሱ በኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት የሲስተም አስተዳደር ባለሙያ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚናገሩት፣ ኮሚሽኑ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በኦንላይ አስደግፎ መስጠት ከጀመረ አንድ ዓመት ሞልቶታል፡፡ ከጥር 2017 ዓ.ም ጀምሮ በየምዕራፍ በመከፋፈል አገልግሎቶችን መስጠት ጀምሯል፡፡ ከአንድ ማዕከል በመጀመር በክትትልና ድጋፍ ዘርፍ እየተሰጠ ይገኛል፡፡
በአንድ ማዕከል ውስጥ ስድስት የሚሆኑ አገልግሎቶች በአዲሱ ሲስተም በኦንላይን አማካኝነት ይሰጣሉ። ወደ አስር የሚደርሱ አገልግሎቶች ደግሞ በክትትልና ድጋፍ ዘርፍ ስር እየተሰጡ ናቸው፡፡ በጥቅሉ 16 የሚሆኑ አገልግሎቶች በአዲሱ ኦንላይን ሲስተም (Addis Ababa Investment Customer management information system) እየተሰጡ እንደሚገኙ አቶ ክንደንጉስ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ቀደም ብሎ የተጀመረ በአንድ መስኮት ወደ አራት የሚደርሱ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ ተደግፈው በመሰጠት ላይ እንደሚገኙም አክለዋል፡፡
በቴክኖሎጂ አገልግሎት መስጠት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአንድ ዓመት በአንድ ማዕከል 7 ሺህ 868 አገልግሎት ተሰጥቷል፡፡ በዚህም ከ35 ሚሊዮን 414 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ በቴሌብር አማካኝነት ተሰብስቧል፡፡ 174 የድጋፍ ደብዳቤ አገልግሎት፣ 800 የሚሆኑ የመስክ እንዲሁም ወደ 2 ሺህ የሚሆኑ በቢሮ ውስጥ ክትትል መደረጉን በሲስተሙ የተመዘገበው መረጃ እንደሚያሳይ የሚናገሩት አቶ ክንደንጉስ፣ ሲስተሙ ተገልጋዮች በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ያላቸው አስተያየትና ቅሬታ ማቅረብ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ እስከ ጥር 5 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ 30 ቅሬታዎች ቀርበዋል። አንዳንዶች ከሲስተም መዘግየት ጋር የተያያዙ ሲሆኑ ሁሉም ቅሬታዎች ተፈትተዋል፡፡
ከተገልጋይ “ሲስተሙ ንቁና ፈጣን አይደለም፤ ቶሎ ምላሽ አለመስጠት ሁኔታ ይታይበታል” በሚል ለተነሳው ጥያቄ አቶ ክንደንጉስ ሲመልሱ፤ “የሲስተም መቆራረጥ አለ፡፡ የእኛ ሲስተም ሰርቨር የሚገኘው የካ ክፍለ ከተማ ካለው የዳታ ማዕከል ነው፡፡ እዚያ ላይ የመብራትና የኔትዎርክ መቆራረጥ ይታያል፡፡ እዚያ ችግር ሲፈጠር ቢሮው የሚሰጠው አገልግሎት ላይ መቆራረጥ ያጋጥማል። ይህንን ለመቅረፍ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረግን ነው፡፡ ከኢትዮ ቴሌኮም የራሳችን ክላውድ ዳታ ሴንተር በመከራየት ለመስራት አቅደናል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅህፈት ቤት ውስጥ የዳታ ማዕከል ስለሚገኝ የካ ያለውን ወደ ከንቲባ ጽህፈት ቤት እንዲዞር ለማድረግ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡” ብለዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር ደንበኞች ቴክኖሎጂውን በአግባቡ መጠቀም እንዲችሉ ባለሙያዎችን በመመደብ ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ እንዲሁም በተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና በተቋሙ ገጸ ድርና ሲስተሙ ላይ እንዴት በቀላሉ መጠቀም እንደሚችሉ በጽሁፍና ምስል እንዲያውቁት ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም ችግር ሲፈጠር ተገልጋዮች ጥቆማ የሚያቀርቡበት ነፃ የስልክ ጥሪ ማዕከል ለማቋቋም እየተሰራ እንደሆነ አቶ ክንደንጉስ ተናግረዋል፡፡
እንደኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሙኒኬሽን ክፍል ቀደም ብሎ የነበረውን አሰራር እንደሚያውቁት የሚናገሩት አቶ ክንደንጉስ፣ በአሁኑ ወቅት ተገልጋዮች የሚፈለገውን መስፈርት አሟልተው ካመለከቱ በአጭር ጊዜ አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ መፈጠሩን አብራርተዋል፡፡
በስንታየሁ ምትኩ