• የተክሎችን እንክብካቤ በተመለከተ በትምህርት ቤቶች ጭምር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ተጠቁሟል
የተፈጥሮ አድናቂ ከሆኑ በቤትዎ ደጃፍ ላይ አልያም ከአጥር ውጭ ያሉ ስፍራዎችን ተጠቅመው የጥላ ዛፎችንና የውበት አትክልቶችን ተክለውበት አልያም ለከተማ ግብርና ሥራ አውለውት ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ላይ ችግኝ መትከል ይህን ማድረግ ስለምንወድ ብቻ የምናደርገው አይደለም፤ የህልውና ጉዳይ ስለሆነም ጭምር እንጂ፡፡ በተለይ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አበረታች እና ለሌሎች ሀገራት ተሞክሮ መሆን የቻሉ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ አዲስ አበባ ያለው እንቅስቃሴ እና ውጤትም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ “ባሳለፍነው ክረምት ላይ የተከልናቸውን ችግኞች በምን ልክ እየተንከባከብናቸው ነው?” የሚለው ግለሰቦችም ሆነ ተቋማት ሊያነሱት የሚገባ ጥያቄ ነው፡፡ የዝግጅት ክፍላችንም በጉዳዩ ላይ የተለያዩ አካላትን አነጋግሯል፡፡
የመሠረት ፋውንዴሽን መሥራች የሆኑት ወይዘሮ መሠረት በትዕዛዙ፣ “ተፈጥሮ ለሰው ልጅ እንደ እስትንፋስ ነው፡፡ በትንሹ እንክብካቤ አድርገን በብዙ በጎ ምላሽ ይሰጡናል፡፡ ‘ሥር ይዘው ራሳቸውን ችለው ከቆሙ በኋላ ምንም ዓይነት እንክብካቤ አያስፈልግም’ የሚለው እሳቤ አሁን አሁን እየቀረ ነው፡፡ እኔም መንግሥት እንዳለማው በፈቀደልኝ በአያትና ሰሚት አደባባይ ላይ የተከልኳቸውን እየተንከባከብኩ ነው” ብለዋል፡፡
“እኔ እያለማሁት ያለው ከድርጅቴ ፊት ለፊት ያለው ስፍራ የኮንስትራክሽን ሥራ የሚሠራበት ቦታ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት የተፈጥሮ አፈር በሲሚንቶ እና በአሸዋ ተሸፍኖ ነበር፡፡ በቦታው ላይ የአረንጓዴ ልማት ሥራ ለመሥራት የግድ አፈር ከመገልበጡ በፊት ቆፍሮ ሲሚንቶና አሸዋውን ማስወገድ ያስፈልግ ነበር፡፡ ይህ በአግባቡ ከተከወነ በኋላ ነው አፈር በመገልበጥ፣ ሣር በመትከል፣ የውበትና የጥላ ዛፎችን የመትከሉ ሂደት የተከናወነው” ሲሉም አብራርተዋል፡፡
ወይዘሮ መሠረት በአስተያየታቸው፤ ከተማን በማስዋብ ሂደት ውስጥ እንደ አንድ ተቋም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በድርጅቱ አጥር ሥር የሚጸዳዱ ብሎም ቆሻሻዎችን የሚጥሉ በርካቶች እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡
አካባቢን ማስዋብ፤ ከጎጂ ነገር መጠበቅ ብልህነትና ወቅቱን የዋጀ ሐሳብ እንደሆነ የሚናገሩት ወይዘሮ መሠረት፣ ተከታታይነት ያለው ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ ናቸው፡፡ ተክሎቹን ለመትከል ቦታ ከመረከብ ባሻገር በየሳምንቱ የተክሎቹን ደህንነት የማረጋገጥ ኃላፊነት ጭምር እንዳለባቸው እና ለዚህም በየሳምንቱ ተክሎቹን ውኃ የሚያጠጡ፣ አፈር የሚያለብሱ እንዲሁም አረሞችን የሚቆርጡ ቁጥራቸው 15 የሚሆኑ አትክልተኞች ቀጥረው እያሠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጭ አቶ ሰለሞን ፀሐይ ይባላሉ፡፡ ነዋሪነታቸው በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የአዲስ መንደር የጋራ መኖሪያ ቤት ባለንብረቶች ማኅበር ውስጥ ነው። ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችን በመሥራት ለአካባቢው ማኅበረሰብ ጭምር ተሞክሯቸውን ማካፈል ችለዋል፡፡ በአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ናቸው፡፡ በተለይ አገር በቀል ዛፎችን፣ የፍራፍሬ ተክሎችን እንዲሁም በከተማ ግብርና ደረጃ የሚለሙትን ተግባራዊ ማድረግ ችለዋል፡፡ እንደ ጎመን፣ ሰላጣ፣ ካሮት፣ ቲማቲም እና ድንች፣ ሎሚ፣ ቡና የመሳሰሉትን መትከል ችለዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ የተተከሉ ችግኞች የጽድቀት መጠናቸው እንዲጨምር በበጋም ጭምር ውኃ በማጠጣት፣ በግቢያቸው አጥር ላይ የተከሏቸውን ደግሞ በአህያ እና በፈረስ እንዳይበሉ ራሱን የቻለ አጥር በማበጀት ጭምር እየተንከባከቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ችግኞችን መትከልና መንከባከብ ባሕሉ ያደረገ ትውልድ ከመፍጠር አንጻር ልጆችን ጭምር ያሳተፈ ሥራ እየሠሩ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ሰለሞን፣ “እያንዳንዱን ድርጊት ስንከውን ልጆቻችንን እንደ አንድ አጋዥ ኃይል መጠቀም ያስፈልጋል። አትክልቶች ሕይወት ያላቸው አካላት እንደሆኑ ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ ለም አፈር ያስፈልጋቸዋል፡፡ መኮትኮት እንደሚያሻቸው ጭምር ካስገነዘብናቸው በቀጣይ ሕይወታቸው ላይ ትልቅ አሻራ እንደማኖር ይቆጠራል” ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ የአረንጓዴ ቦታዎች አያያዝ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ አጥናፉ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት፤ አሁን ባለንበት ወቅት የለሙ አረንጓዴ ቦታዎችን ከመንከባከብ አንጻር የሣር ክርከማ፣ የአረም ማረም፣ ኩትኳቶ፣ ለም አፈር ማኖር፣ ማዳበሪያ ለሚያስፈልገው እንዲሁ ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ ጽድቀቱ ላይ በስፋት መሥራት ተችሏል፡፡ የተተከሉ ችግኞች እንዳይደርቁ በተለይም የውኃ እጥረት እንዳይገጥማቸው ከሕንጻ ሥር እንዲሁም የጉድጓድ ውኃን በፓምፕ በመሳብ፣ በውኃ ማጠራቀሚያ ውኃ በመሙላት እንዲሁም በውኃ ቦቴዎች አማካኝነት ውኃ የማጠጣት ሥራ በባለሙያዎች እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በከተማዋ መዋቅራዊ ማስተር ፕላን መሠረት 30 በመቶ የሚሆነው ቦታ ለአረንጓዴ ልማት የተመላከተ ነው። የለሙ አረንጓዴ ስፍራዎችን ሙሉ ለሙሉ አረንጓዴነታቸውን አስቀጥሎ መሄድ የቢሯችን ተልዕኮ ነው፡፡ ዕፅዋትን የመትከል ሥራ ከተሠራ በኋላ የመጽደቅ ሂደቱን በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት ምልከታ ይደረጋል፡፡ ዕፅዋትን ለማልማት፣ ለመንከባከብ እንዲሁም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ያላቸውን ፍላጎት የሚገልጽ ውል ከተፈራረሙ በኋላ በኃላፊነት ወስደው ያለማሉ፡፡ በየተዋረድ ያለው የሥራ ክፍልም በቼክ ሊስት ይገመግማል፡፡ የደረቁ ችግኞች ካሉ በባለቤትነት ሲንከባከብ የነበረው አካል ችግኙ ወደነበረበት አረንጓዴነት የመመለስ ሥራ እንዲያከናውን ይደረጋል፡፡ በዚህ ሂደት ላይ በየደረጃው ያሉ ባለሙያዎች ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርጉ፣ ግብረ መልስም እንደሚሰጡ ጭምር አቶ ሲሳይ አስታውቀዋል፡፡
ዳይሬክተሩ በማብራሪያቸው፣ መድረክ በማዘጋጀት ተክሎች ከተተከሉ በኋላ በምን አግባብ እንንከባከባቸው በሚለው ዙሪያ በትምህርት ቤቶች ጭምር ለተማሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ካለማንም ጎትጓች ችግኞችን ውኃ ማጠጣት፣ መኮትኮት፣ አላስፈላጊ አረሞችን መንቀል እንዲሁም አፈር የማልበስ ሥራ መሠራትን ይጠይቃል፡፡ ተቋማት ብሎም ግለሰቦች አካባቢያቸው ላይ ያለውን ተክል እንዲንከባከቡ የተለያዩ ብሮሸሮችን፣ በራሪ ወረቀቶችን እንዲሁም በማኅበራዊ ትስስር ገጾች አስተማሪ ጽሑፎችን እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ መሠራቱንም ጭምር አስታውቀዋል፡፡
እንደ አቶ ሲሳይ ገለጻ፤ ከወትሮ በተለየ አግባብ ለመሥራት የታቀደ መሆኑን ተከትሎ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት የሚሰጡ ባለሙያዎች ሳይት ድረስ እየሄዱ ሙያዊ ድጋፍ ያደርጋሉ። በቴክኒክና ሙያ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ላይ ከሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶች ጋር በቀጥታ በሚገናኝ የትምህርት ዘርፍ ሥልጠናዎችን ለማኅበራት፣ ለግለሰቦች ብሎም ለተቋማት ጭምር ይሰጣል፡፡
ሳይንሳዊ አሠራርን በተከተለ አግባብ ማኅበረሰቡ ዘላቂነት ያለው ሥራ እንዲሠራ በትኩረት የምንከታተለው ጉዳይ ነው የሚሉን አቶ ሲሳይ፣ ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሚሰጡንን የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ላይ እንገኛለን። ለሥራችን ተዛማጅነት ያለው በመሆኑ የምርጥ ዘር ምርጫችን ምን መሆን እንዳለበት፣ ችግኞችን እንዴት ማፍላት እንደምንችል፣ የችግኝ አተካከል ቅድመ ተከል ሂደቶችን፣ የእንክብካቤ አግባቦችን እንዲሁም የቦታ አጠቃቀም ምን መሆን እንዳለበት ጭምር ጠንቅቀን በማወቅ ለማኅበረሰቡ ታች ድረስ ባሉ ባለሙያዎች ሙያዊ ትምህርት እንዲሰጥ መደረጉን ጭምር አስታውቀዋል፡፡
በሄለን ጥላሁን