አዲስ አበባ ላይ የተሰሩ የመዝናኛ ሥፍራዎችና የጥበብ ማዕከላት የቱሪስቶች መዳረሻ እንድትሆን ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ተገልጿል
አዲስ አበባ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ መልከ ብዙ ለውጦችን እያሳየች ትገኛለች። ገጽታዋን የሚያጎሉ በተለይም የፓርኮች ልማት፣ የሙዚየሞች ዕድሳት፣ የኮሪደር ልማት ስራዎችና የጥበብ ማዕከላት ከተማዋን ከመኖሪያነት ባለፈ ወደ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻነት እየቀየሯት ነው። በተለይ የተለያዩ የጥበብ ማዕከላትና አዳዲስ የተገነቡት የመዝናኛ ስፍራዎች አዲስ አበባን “የዲፕሎማቲክ መዲና” ከሚለው ስያሜዋ በተጨማሪ “የጥበብና የመዝናኛ ከተማ” እያደረጋት ይገኛል፡፡
ከዚህ ቀደም አዲስ አበባን ቱሪስቶች በዋናነት ወደ ሌላ የሀገሪቱ አካባቢዎች ጉዞ ለማድረግ የሚያልፉባት ከተማ እንደነበረች የአደባባይ ምስጢር ነው። ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ይሄን ዝንባሌ የሚቀይሩ ተግባራት በስፋት በመሰራታቸው የምታስጎበኛቸው ተፈጥሯዊ መስህቦችና ታሪካዊ ቅርሶች እንዲጨምሩ አድርጓል። እንዲሁም መልከ ብዙ የመዝናኛና የኪነ ጥበብ ማዕከላትን መገንባቷ፣ በሚጎበኙ መስህቦቿ ላይ እሴት ጨምራ መምጣቷ ለቱሪዝም ዘርፍ የምታበረክተው አስተዋጽዖ ከፍ እንዲል ቁልፍ ሚና እንዳለው የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በዚህ ወቅት አዲስ አበባ በውስጧ የያዘቻቸው ተፈጥሯዊ መስህቦችና ታሪካዊ ቅርሶች ዘርፈ-ብዙ እየኾኑ መጥተዋል። የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የእንጦጦ እና የአንድነት ፓርኮች፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ የወዳጅነት አደባባይን ጨምሮ እድሳት ተደርጎላቸው ለጎብኚዎች ክፍት የሆኑ መልከ ብዙ የመዝናኛ ሥፍራዎች የጎብኚዎችን ቀልብ መግዛት የቻሉ መስህቦች ናቸው፡፡ የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍልም በመዲናዋ የተሰሩ የኪነ ጥበብ ማዕከላትና መዝናኛ ሥፍራዎች የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃትና ቱሪስቶችን በመሳብ ረገድ ምን አይነት ሚና አላቸው የሚለው ጉዳይ ላይ አጭር ዳሰሳ አድርጓል፡፡
የመዲናዋ አዳዲስ የቱሪዝም ገጸ-በረከቶች
የቱሪዝም ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪና አማካሪ አያሌው ሲሳይ (ዶ/ር)፣ አዲስ አበባ ላይ የተሰሩ እንደ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ ፓርኮችና ሌሎችም የመዝናኛ ሥፍራዎች ቱሪስቶችን በመሳብ ረገድ ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ለዝግጅት ክፍላችን አብራርተዋል፡፡ ቀደም ሲል ቱሪስቶች አዲስ አበባን እንደ መሸጋገሪያ ብቻ ይጠቀሙባት እንደነበር ያወሱት ተመራማሪው፣ አሁን ግን ፓርኮቹን ጨምሮ ታሪካዊ ሥፍራዎቹና የጥበብ ማዕከላቱ ቱሪስቶች ለቀናት በከተማዋ እንዲቆዩ የማድረግ ትልቅ አቅም አላቸው። ይህም የመዲናዋን ገጽታ ከፍ ከማድረግ ባሻገር ለሆቴሎች፣ ለቱሪስት አስጎብኚ ድርጅቶች… ትልቅ ገቢ እንደሚያስገኙ አክለዋል፡፡

እንደ ዶ/ር አያሌው ገለጻ፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተምሳሌት በመሆኑ፣ የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶችና አፍሪካውያንን እየሳበ ይገኛል፡፡ መታሰቢያው ለቱሪዝም ዘርፉ ከፈጠረው ጠቀሜታ ባሻገር እጅግ የምንኮራበት ታሪካዊ ድል የሚዘክር ስለሆነ እንደ ሀገር ያኮራናል፡፡ እንዲሁም እንደ አንድነት ያሉ ፓርኮች መዲናዋ ከመዝናኛነት ባሻገር የምታስጎበኛቸው የታሪክ ቅርሰ ውርሶች መሆናቸው ለቱሪስቶች ምቹ እንድትሆን ያደርጋታል።
አያሌው (ዶ/ር) እንዳብራሩት፣ መዝናኛ ሥፍራዎችና ቱሪዝም የማይነጣጠሉ ናቸው። በእርግጥ ቱሪስቶች ወደ አንዲት ሀገር ሲሄዱ የሚፈልጉት ታሪካዊ ቅርሶችን መጎብኘት ብቻ ሳይሆን የዚያን ሀገር ህዝብ የአኗኗር ዘይቤ፣ ኪነ ጥበባዊ አሻራዎችን፣ ኪነ ሕንጻዎችን እና ሌሎችንም ይጨምራል፡፡ አዲስ አበባ ላይ የተገነቡ ክፍት ሥፍራዎች (ኦፕን ስፔሶች)፣ በእግር ለመንሸራሸር የሚያመቹ ጎዳናዎች፣ ፓርኮችና የኪነ ጥበብ ማዕከላትና ጥበባዊ ሥራዎችን ለማሰናዳት የሚያመቹ ሥፍራዎች… ቱሪስቶች የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ የሚያስችሉ ናቸው፡፡
የኪነት ቱሪዝምን በማጥናት በስፋት የሚታወቁት አድርያን ፍራንክሊን በፈረንጆቹ 2018 ሴጅ ጆርናል በተሰኘ ገጸ-ድር ላይ “Art tourism: A new field for tourist studies” በሚል ርዕስ በጻፉት ጽሑፍ፣ የኪነት ቱሪዝም በዋናነት ኪነ ጥበባዊ ስራዎችና ጥበባዊ አሻራዎችን ለማየት የሚደረግ ጉዞን እንደሚያካትት ጽፈዋል፡፡ ቱሪስቶች ለመዝናናት በበዓላት ወይም በፌስቲቫሎች ላይ ለመታደም የሚያደርጉት ጉዞ የዚሁ የኪነት ቱሪዝም አካል ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ አንድ ሰው ለስራ ወይም ለሌላ ጉብኝት በሄደበት ሀገር ውስጥ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ላይ መታደምን፣ በሀገሩ ያሉ ኪነ ህንጻዎችን መጎብኘትን፣ ኪናዊ የፈጠራ ስራዎችንና የኪነ ጥበብ ሙዚየሞችን መጎብኘት የዚሁ ቱሪዝም አንድ አካል ነው፡፡
በአንድ ሀገር ውስጥ ያሉት የቱሪስት መስህቦች መልክ-ብዙ ናቸው፡፡ ኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎችም ራሳቸውን ችለው የቱሪስት መስህብ ናቸው። እንደ አዲስ አበባ ጉዳዩን ካየነው ደግሞ ለኪነት ቱሪዝም እጅግ የተመቸች ከተማ እየሆነች ትገኛለች፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አዲስ አበባ ውስጥ ተሰርተው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑ መዝናኛ ስፍራዎች ለዚህ ዘርፍ ማደግ የሚኖራቸው ሚና ትልቅ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በቱሪዝም ጉዳይ በመጻፍ የሚታወቀው ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ከዚህ ቀደም ለዝግጅት ክፍላችን በሰጠው አስተያየት አዲስ አበባ ለቱሪስቶች መዝናኛነትና ኪነ ጥበባዊ ሥራዎችን ለመታደም የሚያስችል ዕምቅ አቅም መያዟን አጫውቶናል። የኪነት ቱሪዝም የአንድን ሀገር ባህል፣ እሴትና የሥልጣኔ አሻራዎችን እንደማስተዋወቅ ነው። ለምሳሌ፡- በየዓመቱ ብዙ ጎብኚዎች የጣሊያን ታሪካዊ ከተሞች የሆኑትን ቬነስና ፍሎረንስ የሚጎበኙበት ዋነኛ ምክንያት እዚያ ውስጥ ያሉ የሥነ ህንፃ፣ የዕይታዊ ጥበባት ማዕከላትና የተለያዩ ጥበባዊ የፈጠራ ስራዎችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን በማውሳት አስረድቷል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በመጀመሪያ ጎብኚዎች ወደ አንድ ሀገር ለመጓዝ የሚያነሳሳቸው አንዳች ነገር ሊኖር ይገባል። ታሪካዊ ቅርሶችን፣ ዓመታዊ ፌስቲቫሎችን፣ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶችን፣ የፈጠራ ሥራዎች የሚጎበኝባቸው የጥበብ ማዕከላትን፣ ተፈጥሯዊ መስህቦችን… በአካል ተገኝተው ለመመልከት ሊሆኑ ይችላሉ። ይህን ታሳቢ ያደረጉ መሰረተ ልማቶችና አገልግሎቶች ማመቻቸት ቱሪስቶች እንዲመጡ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ በተለይ አዲስ አበባ ላይ የተሰሩ የመዝናኛ ሥፍራዎችና የጥበብ ማዕከላት መዲናዋ የቱሪስቶች መዳረሻ እንድትሆን ቁልፍ ሚና እንዳለው የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ለዚህ ጥሩ አስረጅ ናቸው፡፡
ጎ ዊዝ ጋይድ ገጸ ድር በፈረንጆቹ ወርሃ ግንቦት 2025 “Tourism In France Statistics 2025: The Ultimate Guide” በሚል ርዕስ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት፣ በፈረንጆቹ 2024 ብቻ 89 ሚሊዮን ቱሪስቶች ፈረንሳይን ጎብኝተዋታል፡፡ የዚህ ስኬት ዋነኛው ምሰሶዎቹ ደግሞ የጥበብ ማዕከሎቿ ናቸው። በፓሪስ የሚገኘው የሉቭር ሙዚየም የጥበብ ማሳያ ብቻ ሳይሆን፣ የፈረንሳይ የቱሪዝም ብራንድ ማህተም ነው። ፈረንሳይ በቱሪስቶች ተመራጭ ያደረጋትም ታሪካዊ ቅርሶችና የጥበብ ማዕከላት ናቸው፡፡

የፈረንሳይ ተሞክሮ እንደሚያሳየው፣ በሀገሪቱ ያሉ የጥበብ ማዕከላት ከከተማ ፕላን፣ ከትራንስፖርት መስመሮች እና ከሆቴል ኢንዱስትሪው ጋር በቀጥታ የተሳሰሩ ናቸው። ጎብኚው ወደ ሙዚየም ሲመጣ ጥበብን ብቻ ሳይሆን ምቾትን፣ ዘመናዊ አገልግሎትንና ታሪካዊ ቅርሶችን አብሮ ያገኛል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ለቱሪዝም እድገት ምቹ የጥበብ ማሳያ ማዕከላት ሲባል የሚከተሉትን መስፈርቶች ማሟላት ያስፈልጋል፡፡ አካል ጉዳተኞችን፣ ህጻናትንና አረጋውያንን ያገናዘበ መሰረተ ልማት፤ ዲጂታል መረጃዎች፣ የድምጽ መመሪያዎች (Audio guides) እና በኢንተርኔት የሚደረግ የቲኬት ግብይት፤ ከመዝናኛና ጥበብ ማዕከላት ጎን ለጎን ያሉ ካፌዎች፣ የስጦታ ዕቃ መሸጫዎች እና ለፈጠራ ባለሙያዎች የሚሰጡ የስራ ቦታዎችን ያካትታል። ፈረንሳይ ይህንን በማሳካቷ የቱሪዝም ዘርፍ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርቷ (GDP) ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ እንዲይዝ አድርጋለች። ከላይ የተጠቀሰው የጎ ዊዝ ጋይድ ገጸ ድር መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በ2024 ከፈረንሳይ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርቷ (GDP) ዘጠኝ በመቶ ድርሻ አስተዋጽኦ ያረገው የቱሪዝም ዘርፏ ነው፡፡
አዲስ አበባም መልከ ብዙ መሰረተ ልማቶችን፣ ፓርኮችን፣ የጥበብ ማዕከላትን፣ የመዝናኛ ሥፍራዎችን ጨምሮ ዘርፉ የሚጠይቃቸውን መስፈርቶች እያሟላች መምጣቷ ቱሪዝሙ እንዲያድግ ትልቅ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል። በተለይም የሳይንስ ሙዚየም እና የዓድዋ ድል መታሰቢያ ለዚህ ማሳያ ናቸው። የፓርኮቹ መገንባት በዙሪያቸው ያሉ ሆቴሎች፣ ካፌዎችና የእጅ ጥበብ ውጤቶች መሸጫዎች ገቢያቸው እንዲጨምር ያደርጋል። ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች መኖራቸው የቱሪዝም ኩባንያዎች በአዲስ አበባ ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈስሱ መተማመንን ይፈጥራል።
በአብርሃም ገብሬ