AMN ጥር 23/2018
የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ያስመዘገቡት አስደማሚ የልማት ስኬቶች ለአፍርካ ቀንድ ቀጣና የኢኮኖሚ ልማት ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጂቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኡመር ጊሌ፣ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ በተገኙበት የአይሻ-2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
በሶማሌ ክልል የተገነባው የአይሻ-2 ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአጠቃላይ 120 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ 80 ሜጋ ዋት ማምረት የሚችለው ምእራፍ በዛሬው እለት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
በምረቃው ላይ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ፤ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በተለያዩ የልማት ዘርፎች ላስመዘገቡት የልማት ስኬት የእንኳን ደስ አላቹህ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ አስደናቂ ስኬት እያስመዘገበች መሆኑንም ገልጸዋል።
ቀጣናዊ ዕድገትን ለማፋጠን በጋራ የምንሰራበት ጊዜው አሁን ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ዘላቂ ሰላምና የመሠረተ ልማት ትስስር ቀጣናዊ ዕድገትን የሚያፋጥኑ አስፈላጊ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን ልማት ለማፋጠን የሚሰጡት ቁርጠኛ አመራር የሀገሪቱ የተፈጥሮ ሃብት ለህዝብ ተጠቃሚነት እንዲውሉ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የውሃና ሌሎች የኃይል አማራጮች ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጩ የልማት ስኬቶችም የአየር ንብረት ተጽዕኖን የሚቋቋም አካባቢ ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና እንዳለው አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ያስመዘገቡት አስደማሚ የልማት ስኬት ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ልማት ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው አብራርተዋል።
በቀጣይም የሶማሊያ ህዝብና መንግስት ከኢትዮጵ የልማት ትሩፋቶች በመጋራት ትብብርን የበለጠ ለማሻሻል በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።