AMN ጥር 23/2018
መንግስት በየአካባቢው ያሉ ሀብቶችን በመግለጥ የሚያከናውናቸው ስራዎች የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጡ መሆናቸውን የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር) ገለጹ።
የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል የሆነው የሸበሌ ሪዞርት ዛሬ በይፋ ተመርቋል።
የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት ሪዞርቱ 15 ኪሎ ሜትር የመንገድ እና 46 ሺህ ስኩዌር ሜትር የመልክዐ ምድር ማስዋብ ስራ መከናወኑን አመልክተዋል።
የእንግዳ መቀበያ፣ ሱቆች፣ ባህላዊ እና ዘመናዊ ምግብ ቤቶች፣ መሰብሰቢያ አዳራሾች፣ አምፊ ቴአትሮችና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ያካተተ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሪዞርቱ የሶማሌ ክልል የኑሮ ዘይቤ እና አኗኗር የሚያሳዩ ባህላዊ ግንባታዎችና የህንጻ ዲዛይኖች ታሳቢ በማድረግ መገንባቱን ነው ያብራሩት።
የፕሮጀክቱ አካባቢ አረንጓዴ የለበሰ እና ጫካ ለማድረግ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ150 ሄክታር በላይ የሚሸፍኑ 360 ሺህ የተለያዩ ችግኞች መተከላቸውንና በርካታ ፍራፍሬዎች ያሉበት ፓርክ እንዲኖረው መደረጉን ጠቁመዋል።
የሸበሌ ሪዞርት ባረፈበት ቦታ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ሲኖሩ ለነበሩ ዜጎች ለመኖሪያ ምቹ የሆነ 24 መኖሪያ ቤቶች ከነቁሳቁሳቸው ተሟልተው እንዲኖሩ የማስቻል ስራም መከናወኑንም አስረድተዋል።
የሶማሌ ክልል አመራሮች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ተቋማት እና ሌሎች አካላት የሪዞርቱ ግንባታ ስኬታማ እንዲሆን ላደረጉት ድጋፍ ሚኒስትሩ አመስግነዋል።
መንግስት በየአካባቢው ያለውን ሀብት በመግለጥ የሚያከናውናቸው መሰል ስራዎች የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።
ከስራዎቻችን ያገኘናቸውን ተሞክሮዎች በመቀመር ለተሻለ ውጤት መትጋት ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።