AMN ጥር 23/2018 ዓ.ም
የሸበሌ ሪዞርት በሁሉም ክልሎች ልማትን ማረጋገጥ እንደሚቻል ማሳያ ነዉ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከገበታ ለትውልድ ዐቢይ ፕሮጀክቶች መካከል ሁለተኛውን እና በ385 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈውን የሸበሌ ሪዞርትን መርቀዉ አገልግሎት አስጀምረዋል፡፡
በምረቃ መርሃ ግበሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የጅቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌን እና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሸክ ሞሃሙድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር የሶማሌ ክልል ከአሁን ቀድም የሚታወቀዉ በግጭትና በጦርነት መሆኑን አንስተዉ አመራሮች ወደ ክልሉ የሚመጡት ለእርቅና ሰላም ለማስከበር እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ዛሬ ግን በሰላም ወዳዱ የሶማሌ ሕዝብ ተሳትፎ በክልሉ በሺህ የሚቆጠሩ መንገዶች፣ የቤት ግንባታዎች እና ሰፋፊ የልማት ስራዎች መከናወናቸዉን ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ የተጀመሩ የጋዝ ፕሮጀክት፣ የነዳጅ ማጣሪያ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የአውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያ፤ የሸበሌ ሪዞርትና የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የልማት ስራዎች በክልሉ በመከናወን ላይ እንደሚገኙም አብራርተዋል፡፡
የሸበሌ ሪዞርት ምረቃ ወጣቶች በታላቅ ተስፋ መሪዎቻቸዉን በደስታ የተቀበሉበትና ሰለም እንደ ዝናብ በሶማሌ ክልል ሲዘንብ ያየንበት እለት ስለሆነ ታላቅ ድልና ስራ ነዉ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል፡፡
የሶማሌን ክልል ከግጭትና ከጦርነት ወደ ልማት ለመለሱ የክልሉ አመራሮችም እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
ሸበሌ ሪዞርት በሁሉም ክልሎች ልማትን ማረጋገጥ እንደሚቻል ማሳያ ነዉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሪዞርቱ የአካባቢዉን ባህል፤ የቤት አሰራር የተከተለ፤ አረንጓዴ ስፍራዎች ያሉበት እና በሺዎች የሚቆጠሩ ዛፎችና ፍራፍሬዎች የተተከሉበት መሆኑን አንስተዋል፡፡
ግንባታዉን በስራ አስኪያጅነት የመሩት የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በወንጪ ያሳዩትን ብቃት በሶማሌ ክልልና በሸበሌ ሪዞርት መድገማቸዉንም አንስተዋል፡፡
የግንባታ ሂደቱ በየትኛዉም ክልል ሰላም፤ ልማትና ፍቅር ባንዲራ ይዞ እስከ መጣ ድረስ እንደ ልጅ የመቀበል ባህል መኖሩ በድጋሚ ያረጋገጠበት ነዉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ