የአገው ፈረሰኞች በዓል የኢትዮጵያን ነጻነት፣ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትና የታሪክ ትሥሥር የሚያሳይ ሕያው ሙዝየም ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

You are currently viewing የአገው ፈረሰኞች በዓል የኢትዮጵያን ነጻነት፣ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትና የታሪክ ትሥሥር የሚያሳይ ሕያው ሙዝየም ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

AMN ጥር 23/2018

የአገው ፈረሰኞች በዓል የኢትዮጵያን ነጻነት፣ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትና የታሪክ ትሥሥር የሚያሳይ ሕያው ሙዝየም መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

86ኛው የአገው ፈረሰኞች በዓል ”የአብሮነት ቅርስ፤ የሰላም ውርስ” በሚል መሪ ሀሳብ በአዊ ዞን እንጅባራ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአገው ፈረሰኞች በዓል የኢትዮጵያን ነጻነት፣ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትና የታሪክ ትሥሥር የሚያሳይ ሕያው ሙዝየም ነው ብለዋል።

ፈረስ በአገው ሕዝብ ዘንድ ካለው ማኅበራዊ ፋይዳ ባሻገር ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ነጻነት በዋለው ውለታ ትልቅ ስፍራ እንደሚሰጠው ተናግረዋል።

ቅድመ አያቶች ፋሺስት ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ የከፈተውን ወረራ ”በፈረስ ጉልበት በጦር አንደበት” በሚል የጀግንነት ወኔ በተጎናጸፉት ድልም የፈረስ ወለታ የሚዘነጋ እንዳለሆነ ገልጸዋል።

በተለይም የአዊ ፈረሰኞች ከዓድዋ ድል ጀምሮ ወራሪዎችን መሸሸጊያ በማሳጣት ረገድ የነበራቸው የነፃነት ዓርማነት ሚና የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።

የፈረስ ታሪክ የሁላችንም ታሪክ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ፈረስ ሰሜኑን ከደቡብ፣ ምሥራቁን ከምዕራብ በማስተሳሰር ኅብረ-ብሔራዊት ኢትዮጵያ በመገንባት ሂደት ጉልህ ድርሻ እንዳለው አስረድተዋል።

የአገው ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማውን ከፈረሱ በላይ ከፍ አድርጎ የሚያሳይ፣ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ኩሩ ሕዝብ መሆኑን ገልጸዋል።

የአዊ ሕዝብ ጽንፈኝነትን እና ጎጠኝነትን እምቢ በማለት ሰላሙን በራሱ እጅ ማስከበር የቻለ አርዓያ ሕዝብ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አዊ ዞን 9 ወንዞች የሚገማሸሩበት፣ ዘንገናና ጥርባ ሐይቆች የሚንፈላሰሱበት፣ ደኖችና ዋሻዎች የሞሉበት ምድር መሆኑንም አንስተዋል።

ይህንን ተፈጥሯዊ ፀጋ በሰላም ጠብቆ ወደ ሀብት መቀየር ከተቻለ፣ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም የሚተርፍ ብልጽግና ይገኝበታል ብለዋል።

ሰላምን በማስጠበቅ ከሌሎች የሀገራችን ሕዝቦች ጋር በኅብረ ብሔራዊ አንድነት ኢትዮጵያን አጽንተን እንቀጥላለን ብለዋል።

ጽፈኝነትንና ጎጠኝነትን ታግለን፤ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽና ተምሳሌት ለማድረግ ለተቀመጠው የጋራ ግባችን በጋራና በጽናት መትጋት አለብን ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ፈረሶቻችን ከዓድዋ እስከ እዚህ አድርሰውናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ እኛ ደግሞ ሁለንተናዊ ብልጽግናዋን እውን ያደረገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማውረስ መትጋት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የአገው ፈረሰኞች በዓል የኢትዮጵያን ነጻነት፣ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትና የታሪክ ትሥሥር የሚያሳይ ሕያው ሙዝየም መሆኑን ተናግረዋል።

የአገው ፈረስ በዓል በዓለም ቅርስነት በዩኔስኮ እንዲመዘገብ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣንና የሚመለከታቸው አካላት በባለቤትነት እየሠሩ መሆኑን አንስተው፣ ይህም በቅርቡ እንደሚሳካ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review