የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማት የጎረቤት ሀገራትን ትስስር መሰረት ያደረገ ነው -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

You are currently viewing የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማት የጎረቤት ሀገራትን ትስስር መሰረት ያደረገ ነው -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

AMN ጥር 23/2018

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጁቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኡመር ጊሌ፤ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ በተገኙበት የአይሻ- 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።

በሶማሌ ክልል የተገነባው የአይሻ 2 ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአጠቃላይ 120 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ 80 ሜጋ ዋት ማምረት የሚችለው ምእራፍ በዛሬው እለት አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ልናረጋግጠው የምንፈልገው እድገት አጠቃላይ የዓለም የኢኮኖሚ ጉዞን ከግምት ያስገባ ነው ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ የእድገት መሰረቶችን በመለየት ለውጤታማነት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህም ውስጥ የኃይል መሰረተ ልማት ዋነኛው መሆኑን ተናግረዋል።

የኃይል ልማታችን ከአከባቢ እንክብካቤ ጋር የተናበበ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ደግሞ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁነኛ ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያዊያን ሃብት ብቻ የተገነባ ፤ለእኛ ለአፍሪካዊያን ኩራት ፤ ለዓለም ደግሞ ምሳሌ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማት የጎረቤት ሀገራትን ትስስር መሰረት ያደረገ ስለመሆኑ ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ከጂቡቲ ጋር በኃይል ብቻ ሳይሆን በውሃና ክፍያ መንገድ ጭምር መተሳሰሯን ተናግረዋል።

በቀጣይም ከሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ጋር በኃይል ለመተሳሳር እየሰራች መሆኑን አብራርተዋል።

ዛሬ የተመረቀው የአይሻ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫም ይህን ትስስር ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።

ኢትዮጵያ በተለይ በታዳሽ ኃይል ልማት እያከናወነች ያለው ስራ ለኮፕ 32 እንድትመረጥ እንዳደረጋትና ፤ ኢትዮጵያ ጉባኤውን አፍሪካን በሚያኮራ አግባብ ለማዘጋጀት እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ትልቅ አቅም ያለበት አካባቢ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የቀጣናው ሀገራት ይህንን አቅም በተደመረ መንገድ መጠቀም ከቻሉ ከራሳቸው አልፎ ሌሎችን ወደ መርዳት እንደሚሸጋገሩ ተናግረዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review