AMN – ጥር 24/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማሳካት ኢትዮጵያውያን ተመሳሳይ ግንዛቤ እና የጋራ አቋም ሊኖራቸው እንደሚገባ የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ የብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የውጭ ግንኙነት ማዕከል አድርጎ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
በዋናነት ብሔራዊ ጥቅሞችን ለሕዝብ በሚገባ ማስረዳት እና አጀንዳዎቹን በማሳካት ሒደት ውስጥ ኢትዮጵያዊያን የብሔር፣ የማንነት እና የሃይማኖት ልዩነት ሳይገድባቸው የጋራ አቋም እንዲይዙ በሚዲያ እና የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ በርካታ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሜ ነው ብላ አቋም የያዘችበትን ጉዳይ ለማሳካት የሚያስችል የተደራጀ ውስጣዊ አቅም እየገነባች መሆኑን የገለጹት ኃላፊው ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቅ አንድ ማሳያ ነው ብለዋል።
በተባበረና የጋራ አስተዋጽዖ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንደሚኖራት ጥያቄ የለውም ያሉት ኃላፊው የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት እና ሕዝቡ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖረው ብሎም ለስኬቱ እንዲረባረብ እና በዓለም አደባባይ ተቀባይነት እንዲኖረው መደረጉ ትልቅ ውጤት መሆኑንም ተናግረዋል።
በዓለም አደባባይ ተፈላጊ የሆነችው ኢትዮጵያ ባላት የዲፕሎማሲ አቅም የዓለም የንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል እያደረገች ያለችው ጥረት እተሳካ መሆኑን ጠቁመው ይህም የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳዎቻችን ስኬት ማሳያ ነው ብለዋል በቆይታቸው።
ገዢው የብልጽግና ፓርቲ በሀገር አቀፍ እና በክልል ደረጃ በዘረጋቸው የሚዲያ እና የሕዝብ ግንኙነት አደረጃጀቶች ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃዎችን በማቅረብ ኅብረተሰቡ እየተከናወነ ያለውን የልማት ሥራ እንዲገነዘብ እና እንዲደግፍ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።
በትዝታ መንግስቱ