ስምና ታሪኩ የሰመሩለት ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ

You are currently viewing ስምና ታሪኩ የሰመሩለት ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ

AMN- ጥር 24/2018 ዓ.ም

በደጃዝማች ገረሱ ዱኪ መኖሪያ ቤት ላይ የተገነባው አዲስ ከተማ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ስያሜውን ወደ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ለውጧል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የነዋሪዎችን ህይወት የሚያዘምኑ ግንባታዎችን ከማከናወን ባለፈ፣ ለሀገር ነፃነት ደማቸውንና አጥንታቸውን የገበሩ፣ ነገር ግን በታሪክ መዝገብ ውስጥ ለዘመናት ተዘንግተው የቆዩ ጀግኖችን ዳግም እያስታወሰ ለትውልድ አርአያ እንዲሆኑ እያደረገ ነው።

አዲስ አበባ በአፍሪካ ውስጥ የቅኝ ገዢዎች አሻራ የማይታይባት፣ ዜጎቿ መስርተው ለርዕሰ መዲናነት ያበቋት እና የነፃነት ተምሳሌት የሆነች ብቸኛ ከተማ ስለመሆኗ ብዙዎች ይስማሙበታል።

ይህች ግዙፍ ታሪካዊት ከተማ ታዲያ ለስሟ የሚመጥኑና ከታሪኳ የሚስተካከሉ የመዝናኛ አማራጮችን ስትገነባ፣ የነዋሪዎቿን የእለት ተእለት እንቅስቃሴ የሚያዘምኑ ማህበራዊ ተቋማትንም ስታንፅ ትላንቷን ላለመዘንጋት ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርጋለች።

የትላንት ባለውለታዎቿንም በማሰብ፤የቀድሞው አዲስ ከተማ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ስያሜው ወደ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ እንዲለወጥ በማድረግ፣ ትውልድ ከጀግኖች የሀገር ፍቅርና ጀግንነት እንዲማር መንገድ አመቻችታለች።

የቀድሞው አዲስ ከተማ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ በታላቁ አርበኛ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ስም መሰየሙም የዚህ ታላቅ ሀገራዊ እውቅና ማሳያ ሆኗል።

ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ የሀገር ነፃነትን ጠብቀው ካቆዩ የኢትዮጵያ ባለውለታዎች መካከል አንዱ ናቸው።

መድፍና መትረየስ ጥይት ሲጓረሱ አሳላፊ ነበር የማሩ ገረሱ የተባለላቸው ገረሱ ዱኪ፣ በ1928 ዓ.ም በማይጨው ጦርነት ከፍተኛ ጀብዱ ፈፅመዋል።

ከ1929 እስከ 1933 ዓ.ም ደግሞ አርበኞችን በመምራት የኢትዮጵያን ነፃነት አቅርበዋል።

ለዚህም ነው ትውልድ ጀግንነትን እያስታወሰና የሀገር ፍቅርን እያሰበ እንዲማር፣ በመኖሪያ ቤታቸው ላይ የተገነባው አዲስ ከተማ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ በስማቸው እንዲሰየም የተደረገው።

ሀገር ወዳድ ትውልድ መገንባትና ትላንትን ከዛሬ ጋር አስተሳስሮ ነገን መሟገት የከተማ አስተዳደሩ ፍላጎት መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ዳግማዊት ግርማ ለኤ ኤም ኤን ተናግረዋል።

ወይዘሮ ዳግማዊት አክለውም፣ መንግስታችን ምን ያህል የተረሱትንና የተዘነጉትን እያስታወሰ እንዳለ የሚያሳየን ትልቅ ተግባር ነው ብለዋል።

ታሪክን ማውሳት፣ ታሪክ የሰሩ ሰዎችን ማሰብና ጀግንነታቸውን ማወደስ ለዛሬው ትውልድ የሚያስተላልፈው ትልቅ መልእክት አለ።

ዛሬ ላይ እኛ አርበኛ የምንሆነው ኢትዮጵያን ሊያሻግር የሚችል ትውልድ በመቅረፅ ስለሆነ፣ ይህ ተቋም የሚገባውን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል ሲሉም የአደራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ዲን አቶ መስፍን ቸሩ በበኩላቸው፣ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ሕይወታቸውን ለሀገር መገበራቸውን አንስተዋል።

የሰው ልጅ ለሀገሩ ህይወቱን እስከ መስጠት የሚሰዋ ከሆነ፣ እኛ ደግሞ በእውቀት ራሳችንን አብቅተን ክህሎት ያላቸው ዜጎችን በማፍራት፣ ችግር ፈቺ ትውልድን መቅረፅ ይኖርብናል ያሉት አቶ መስፍን፣ ኮሌጁ በደጃዝማች ገረሱ ዱኪ መሰየሙም ለዛ ትልቅ ጉልበት ይሆነናል ሲሉ ገልጸዋል።

ለእኚህ ጀግና አርበኛ በስማቸው ተቋም መሰየሙ ለዘመን ተጋሪዎቻቸውም ልዩ ስሜት ፈጥሯል።

የ103 ዓመቱ አርበኛ መኮንን መሸሻ፣ ይህን ግቢ በዚህ መልኩ በማየቴ ፈጣሪዬን አመሰግናለሁ ብለዋል።

ደጃዝማች ገረሱ እንደቀላል ሰው የሚታዩ አይደሉም ያሉት አርበኛ መኮንን፣ እንዲያውም ይህ ክብር ሲያንሳቸው ነው በማለት ገልጸዋል።

በ1897 ዓ.ም የተወለዱት ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ፣ በ1958 ዓ.ም በ61 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review