AMN -ጥር 25/2018 ዓ.ም
12ኛው የኅብረት ሥራ ማህበራት ሲምፖዚየም በአድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ይገኛል። ሲምፖዚየሙ የዘርፉን እድገት፣ ሀገራዊ አበርክቶ እና ፈተናዎች የሚዳስሱ ጥናታዊ ፁህፎች ቀርበውበታል።
ህብረት ስራ ማህበራት በተለይም በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት የሚያጋጥም የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ከፍ ያለ አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ሲምፖዚየሙን የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ተናግረዋል።
የማህበራቱ አቅም እንዲያድግና የገበያ ስርዓቱ በህብረት ስራ ማህበራት እንዲበየን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ስለመሆኑም ምክትል ከንቲባው አብራርተዋል። የፋይናንስ ተቋማትም ህብረት ስራ ማህበራትን መደገፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ሀገር የጀመረችውን ከተረጂነት የመላቀቅ ጥረት በመደገፍ ረገድ ህብረት ስራ ማህበራት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ያነሱት ደግሞ የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌትነት ታደሰ ናቸው።
ማህበራቱ ፍትሀዊ የገበያ ስርዓት ለመዘርጋት እና በሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ የሚጫወቱትን ሚና ለማሳደግ ሲምፖዚየሙ አስፈላጊ ስለመሆኑ የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሽታዬ መሃመድ አብራርተዋል።
ሲምፖዚየሙ “ኅብረት ሥራ ከምርት እስከ ግብይት፤ ከአምራች እስከ ሸማች” በሚል መሪ ሃሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።
በካሳሁን አንዱዓለም