ሁሉም የመንግስት አገልግሎቶች ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ይገባሉ

You are currently viewing ሁሉም የመንግስት አገልግሎቶች ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ይገባሉ

AMN ጥር 25/2018

በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ሁሉም የመንግስት አገልግሎቶች ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንደሚገቡ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለም ፀሐይ ጳውሎስ ገለጹ።

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ የሆኑ አስፈጻሚ ተቋማት የ2018 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት አፈጻጸም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት ተገምግሟል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለም ፀሐይ ጳውሎስ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ለዜጎች የተቀላጠፈ እና ከብልሹ አሰራር የጸዳ አገልግሎት ለመስጠት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሚናው የጎላ ነው።

ይህንንም እውን ለማድረግ በፌደራል ተቋማት የሚሰጡ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የማስገባት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁንም አገልግሎቶችን ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ስርዓት ከማስገባት አንጻር ውስንነቶችን መኖራቸውን ገልጸው፤ ይህን ለመቅረፍ በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ሁሉም የመንግስት አገልግሎቶች ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲካተቱ ይደረጋል ብለዋል።

በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በኦንላይን መሰጠት የሚገባቸውን አገልግሎቶች እንዲሁም በአካል መሰጠት ያለባቸውን አገልግሎቶች በማእከሉ መሰጠት የሚቻልበትን አቅም መፍጠር አለብን ብለዋል።

እቅዱም እውን እንዲሆን የሚመለከታቸው ተቋማት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ሚናቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review