እሱን የገጠመው ችግር በሌሎች ላይ እንዳይደርስ ፋውንዴሽን ያቋቋመው ወጣት

You are currently viewing እሱን የገጠመው ችግር በሌሎች ላይ እንዳይደርስ ፋውንዴሽን ያቋቋመው ወጣት

AMN -ጥር 25/ 2018 ዓ.ም

ኑሮ ያልጠበቅነው ፈተናን ያጋፍጠናል፣ አንዳዶች ሲወድቁ፣ አንዳዶች ደግሞ ከችግር ውስጥ በብርታት ይወጣሉ። በረከት በቀለ ከብርቱዎቹ ይጠቀሳል።

በረከት ሲወለድ እንደብዙዎቹ ህፃናት ከሙሉ ጤንነት ጋር አልነበረም። ከልጅነቱ ጀምሮ አብሮት ያደገው በሽታ ከሰው መቀላቀልን ፈታኝ ቢያደርገበትም ተሸብቦ ከቤት አልቀረም። ይልቁንም ችግሩን ባደባባይ በመግለፅ ሌሎች ድጋፍ እንዲያገኙ ግንዛቤ እየፈጠረ ይገኛል።በማሕበራዊ ሚዲያም ሚስተር ዳይፐር የሚል ቅፅል ስም አግኝቷል።

በረከት የ”ስፓና ቢፊዳ” ችግር ተጠቂ ነው። ስፓይና ቢፊዳ የጀርባ አጥንት መከፈት ችግር ሲሆን በእርግዝና ወቅት ፎሊክ አሲድ አለመውሰድ፣ የጨረር ተጋላጭነት በመሳሰሉት እንደሚከሰት ይጠቀሳል።

በዚህ በሽታ ምክንያት በረከት መፀዳጃ አካላቱ መቆጣጠር ስለማይችሉ፣ ዳይፐር መጠቀም ግዴታ ነው። በዳይፐር እጦት እንቅስቃሴው ታጉሉ ከቤት ውሏል፣ ሰዎችም ሲጠየፉት አልፏል።

ወጣቱ በረከት ይህ ችግር አሸማቆ ሳያስቀረው፣ በቤተሰቡና በፍቅረኛው አብሮነት እየታገዘ ትምህርቱን አጠናቋል። በነርሲንግ 3.99 ከፍተኛ ነጥብ በማምጣት፣ የወርቅና ዋንጫ ተሸላሚ ሆኖ ነው የተመረቀው።

ያለቤተሰቡ ድጋፍ ለውጤት ሊበቃ እንደማይችል የሚናገረው በረከት፣ ፍቅረኛው እውነታውን ሲነግራት ሳትጠየፍ ከጐኑ ሆና ችግሩን ለማቃለል ማገዟም ብርታት ሆኖታል።

“መኖር ማለት መቆረስ ነው፤ ለሌሎች መትረፍ ነው” የሚለው ወጣት በረከት፣ ኪም ቢፊዳ የተሰኘ ፋውንዴሽን እየመሰረተ መሆኑንና በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ከኤ.ኤም.ኤን “ቀን አዲስ” መሰናዶ ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጿል።

ስፓይና ቢፊዳ በሽታ ላይ ግንዛቤ በመፍጠር፣ ይህ ችግር ያለበት ሕፃን ከዚህ በኋላ እንዳይወለድ፣ የተወለዱትም ድጋፍና ክትትል እንዲያገኙ ማስቻል የበረከት ህልም ነው።

ስፓና ቢፊዳ በሽታ በህክምና ሙሉ ለሙሉ ማዳን ባይቻልም፣ በተወሰነ ደረጃ ሕመሙንና ተዛማጅ ችግሮችን መቀነስ ይቻላል።

ነገ እሞታለሁ በሚል ሰቀቀን ውስጥ ማለፉን ያልሸሸገው በረከት፣ አሁን ብሩህ ተስፋን ያማትራል።

የራሱን ኑሮ ከማደላደል ባለፈ ለሌሎች በማገዝ ድርሻዬን መወጣት አለብኝ የሚል ፅኑ አቋም እንዳለው ነው የገለፀው።

ከዚህም ባለፈ “ኪም ዳይፐር “በሚል የዳይፐር ኩባንያ የማቋቋም ሕልም እንዳለውም ነው በረከት በቀለ የተናገረው።

በታደሰ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review