የኢትዮጵያ ታምርት ስኬት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ አነቃቅቷል

You are currently viewing የኢትዮጵያ ታምርት ስኬት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ አነቃቅቷል

AMN – ጥር 26/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ባሳየው አስገራሚ መነቃቃት፣ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የዘርፉ የውጭ ምንዛሬ ግኝት (Export) ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ እንደሚያድግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ፤ “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ የፋብሪካዎች የማምረት አቅም ከ47 በመቶ ወደ 66.3 በመቶ ከፍ ማለቱንና ዘርፉ አዲስ ተስፋ እየሰነቀ መሆኑን አብስረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው እንዳመለከቱት፣ በቅርቡ በተካሄደው የንግድ ቆጠራ መሠረት በኢትዮጵያ ከግብርና ውጭ 2.6 ሚሊዮን የንግድ ተቋማት ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 413 ሺህ (17 በመቶ) የሚሆኑት አምራች ኢንዱስትሪዎች ናቸው።

ይህ አሀዝ መንግስት የዘርፉን ጥንካሬና ድክመት ለይቶ ድጋፍ እንዲያደርግ ትልቅ አቅም መፍጠሩን ገልጸዋል።

በተለይም ጥራት ያላቸውና ግዙፍ ኢንቨስተሮችን ወደ ሀገር ውስጥ የማስገባት ስትራቴጂ ውጤት እያመጣ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከቬትናም የመጣው ቶዮ (Toyo) የተሰኘው የሶላር ኩባንያ በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ 66 ሚሊዮን ዶላር ኤክስፖርት ማድረጉን ጠቅሰዋል።

ይህ አንድ ኩባንያ ያስመዘገበው ውጤት በአንዳንድ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ካሉ በርካታ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ድምር ውጤት እንደሚበልጥም አብራርተዋል።

በ ኢትዮጵያ ታምርት መርህ በተከናወኑ ተግባራት፣ ቀደም ሲል ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ረገድ ትልቅ ስኬት ተመዝግቧል።

በዚህም እስካሁን 3.4 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ተችሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢንዱስትሪ ዘርፍ በቢሊዮን የሚቆጠር ኤክስፖርት እናስመዘግባለን ብለዋል።

ከማኑፋክቸሪንግ በተጨማሪ የማዕድን ዘርፉ ባለፉት ስድስት ወራት የ30 በመቶ እድገት ማሳየቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የብረት ምርት በ36 በመቶ እንዲሁም የሲሚንቶ ምርት በ28 በመቶ መጨመሩን ገልጸዋል።

ይህም በሀገሪቱ ያለውን ከፍተኛ የቤት ግንባታ ፍላጎት ለመመለስ እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review