AMN — ጥር 26 ቀን 2018 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ወደብን የመጠቀም ፍላጐቷ ለብሔራዊ ደኅንነቷና ለህልውናዋ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ሀገሪቱ ከቀይ ባሕር ጋር ያላትን ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ ትስስር በዝርዝር ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ሰፊ የሕዝብ ቁጥር ያላት ሀገር እንደመሆኗ፣ የባሕር በር ማግኘቷ ለህልውናዋ ወሳኝ ሲሆን፤ ይህንንም ለማሳካት በሰላማዊ ድርድር እና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ስምምነት መደረግ እንዳለበት ገልፀዋል።

ለዚህም ኢትዮጵያ እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን በባለቤትነት ማጋራት ወይም በሊዝ በመስጠት ለመደራደር ዝግጁ መሆኗን ጠቁመዋል።
ቀደም ሲል በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል በነበረው ግጭት ሰላም በወረደበት ወቅት ኤርትራውያን በኢትዮጵያ የነበራቸውን ንብረት መልሰው ማግኘታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰው፣ ኢትዮጵያም በኤርትራ መሬት ላይ የገነባቻቸው ወደቦች እና መሠረተ ልማቶች በዚሁ መንፈስ ሊታዩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ 13ዐ ሚሊዮን ሕዝብ ይዛ ለሁሉም ጐረቤት ሀገራት እዳ መሆን የለባትም፤ የባህር በር የመጠቀም ፍላጐቷን በሰላማዊ መንገድ በድርድር ለመጨረስ ፍላጐት እንዳላትም አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ይህን ካላሳካች ያሰበችው ብልፅግና ልታሳካ እንደማትችልም ገልፀዋል፡፡
በበረከት ጌታቸው