ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር በጋራ ለመልማት ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ነው – ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር በጋራ ለመልማት ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ነው – ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ጥር 26/2017 ዓ.ም

በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የሚገኙ ህዝቦች በቋንቋ እና በባህል እጅግ የተሳሰሩ ናቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመንግሥትን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም በሚመለከት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል

በአባላቱ ከተነሱ ጉዳዮች አንዱ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳይ ሲሆን ለጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ኢትዮጵያ በቀጣናው እና ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅሟን መሰረት ባከበረ መልኩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የቀጣናው ሃገራት በትብብር ብሔራዊ ጥቅማቸው ከማስከበር ይልቅ የሌሎች ሀይሎች ጉዳይ አስፈጻሚ ሆነው መቆየታቸው ተገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ እንዳይቀደድ የተሰፋ፤ እንዳይጣመር የተቀፈደደ አካባቢ ነው ብለዋል፡፡

በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የሚገኙ ህዝቦች በዘር፣ በቋንቋ እና በባህል እጅግ የተሳሰሩ ናቸው። ሆኖም ግን፣ በአካባቢው የሚታየው ከፍተኛ የውጭ ሀይሎች ጣልቃ ገብነት እና ፉክክር ቀጠናው ካለው ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚ እንዳይሆን እንቅፋት ሆኗል ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎረቤት ሀገራት አንዱ ለሌላው መከታ መሆን ሲገባቸው፣ ለችግር እና ለጥይት መቀባበያነት መጋለጣቸውንም አንስተዋል ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፉት ስድስት ወራት በኢትዮጰያ በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡

ኢትዮጵያ በ17ኛው የብሪክስ ጉባኤ መሳተፏንና፤ እንደ ብሪክስ አባልነቷ በተለይም በአለምአቀፍ ውሳኔ ሰጪ መድረኮች ለአዳዲስ ገበያዎች እና በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ሰፋ ያለ ውክልና በሚገኝበት ሁኔታ ላይ በንቃት አስተዋፅኦ እያደረገች መሆኑን ገልፀዋል ።

በሩሲያ በተዘጋጀው የዓለም የአቶሚክ ሳምንት ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያም ተሳታፊ እንደነበረች ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በኃይል ማመንጫ፣ በግብርና፣ በጤና ልማት እና የመከላከያ ትብብርን ጨምሮ ሰፊ ጉዳዮች ላይ ውይይት የተደረገበትና ዲፕሎማሲያዊ ዓቅም የደረሰበትን ደረጃ ያሳየ እንደነበር ይታወቃል ።

በውይይቱ ለማኅበረሰብ አገልግሎት የሚውል የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ የማልማት ስምምነቶችን ጨምሮ የጋራ ፍላጎት በሆኑ ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ስራዎች የተሰሩበት እንደነበርም ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት በተካሄደው የቡድን 20 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያን ስትራቴጂካዊ ጥቅም የሚያጸኑ የሁለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ተግባራትንም አሳክተዋል።

ሌላኛው ኢትዮጵያ በኬንያ ናይሮቢ በተካሄደው 24ኛው የCOMESA የመሪዎች ጉባኤ ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ዲጂታላይዜሽንን ለቀጣናዊ የእሴት ሰንሰለት መጎልበት በመጠቀም ለዘላቂ እና አካታች ዕድገት ማዋል” በሚል ጭብጥ በተካሄደው በዚሁ ጉባኤ ላይ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የአፍሪካን የኢኮኖሚ ታሪክ የመቀየር ልዩ እድል ላይ አፅንኦት ሰጥተው አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቡድን 20 ጉባኤ ላይ ከመሳተፋቸው ጎን ለጎን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፣ የአለም ባንክ ፕሬዝደንትን ጨምሮ ከበርካታ ሀገራት መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ፤ ቀጣናዊ፤አህጉራዊ እና ዓለም ዓቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸው የሚታውስ ነው፡፡

ይህም ኢትዮጵያ ለክልላዊ ትብብር እና መረጋጋት እያሳየች ያለውን ቁርጠኝነት አጉልቶ ያሳያል። እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለይፋዊ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የመጡትን የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይን ተቀብለው የወል ፍላጎት በሆኑ የሁለትዮሽ ግንኙነቶች እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ማገባድጃ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጂቡቲ እና የሶማሊያ መሪዎችን በጅግጅጋ አየር ማረፊያ ተቀብለው አነጋግረዋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የዩናይትድ ኪንግደም የኮመንዌልዝ፣ ልማት ጉዳዮች እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይቬት ኩፐርን አግኝተው በቁልፍ የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

በመሆኑም ያለፉት ስድስት ወራት እንደ ሃገር በተከናወኑ ዲፕሎማሲያዊ ሰራዎች ሰኬት የተመዘገበበት እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስርት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በህዝብ ተወካዮች መክር ቤት በነበራቸው ቆይታ ያብራሩ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሃገራት ጋር በጋራ ለመልማት ያላትን ፍላጎት በጉልህ ያሳየ መሆኑን አብራርተዋል ፡፡

በቶለሳ መብራቴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review