AMN ጥር 27/ 2018 ዓ.ም
በጄኔራል ተፋሂ ላይድ የሚመራ የአልጄሪያ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ልዑክ በኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና የልምድ ልውውጥ ጉብኝት አካሂዷል።
የልዑካን ቡድኑ አባላት በዩኒቨርሲቲው ያለውን ወታደራዊ የምርምር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራዎችን ተዟዙረው ምልከታ እና የልምድ ልውውጥ አድርገዋል።
ጉብኝቱ በኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ እና በአልጄሪያ ጦር ኮሌጅ መካከል ያለውን የጋራ ትስስር፣ የእውቀት ሽግግር እና ዘላቂ ትብብር ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድግ ተገልጿል።
በጉብኝቱ ልዑካኑ በኢንጂነሪንግ ኮሌጅ: የምህንድስና ኮሌጅ: የኤሌክትሪክ ፖወር እና የኤሮኔቲካል ምህንድስና ላቦራቶሪዎችን በተግባር ጎብኝተው የሚከናወኑ ሳይንሳዊ እና ቴክኖሎጂያዊ የምርምር ውጤቶችን ተመልክተዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ኘሬዝዳንት ብርጋዲየር ጄኔራል ከበደ ረጋሳ ልዑካን ቡድኑን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ይህ ጉብኝት እና ልምድ ልውውጥ እንደ አፍሪካ አህጉር የጋራ የመከላከያ እውቀትና የሰላም ግንባታ ራዕይን የሚያጠናክር ታሪካዊ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።
የልዑካን ቡድኑን የመሩት ጄኔራል ተፋሂ ላይድ
የተመለከትነው በሙሉ የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ በአፍሪካ የወታደራዊ ትምህርት እና የምርምር መሪ ተቋም መሆኑን የሚያረጋግጥ ግልፅ ምልክት ነው ሲሉ አድናቆታቸውን ገልፀዋል።
ዘመናዊ መከላከያ በጦር ብቻ አይገነባም፤ በእውቀት፣ በሳይንስ እና በጠንካራ አለምአቀፍ ትብብር ይጠናከራል። ይህ ጉብኝት የጋራ እንደ አህጉር ያለውን ወታደራዊ የምርምር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር አቅም የሚያሳድግ መሆኑ በጉብኝቱ መገለጹን የሃገር መከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለኤኤምኤን የላከዉ መረጃ ያሳያል።