AMN ጥር 27/2028 ዓ.ም
6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባዉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፌዴራል መንግስት የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጤና ዘርፍን በተመለከ ባነሱት ምላሽና ማብራሪያ፣የምርት ችግር በመድኃኒት አቅርቦት ላይ እንደሚስተዋል አንስተው፣ከጥቂት አመታት በፊት ስምንት በመቶ ይመረት የነበረው የሀገር ውስጥ ፍጆታ ምርት አሁን ላይ አርባ ሁለት በመቶ በመድረስ ትልቅ እመርታ አሳይቷልም ብለዋል።

በህክምናው ዘርፍ ዲጂታላይዜሽን ጀምረናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣”ጤና እቴጌ” የሚባል መተግበሪያ ይሄን ችግር መፍቻ ተብሎ የበለፀገ መሆኑንም አንስተዋል።
ይህም በዲጂታል የመረጃ ልውውጥ ከፍተኛ እመርታ እንዲመጣ አስችሏልም ብለዋል።
ለዓብነትም በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች ከሃያ ሰባት በመቶ ወደ 61 በመቶ ዕድገት ሲያሳይ፣ከመቶ ሺህ ከሚወልዱ እናቶች አራት መቶ ገደማ ይሞት የነበረው ወደ መቶ አርባ አንድ እንዲቀንስ ያስቻለ መሆኑን አብራርተዋል።
ይህም ከአምስት አመት በታች የእናቶችና የህጻናት ሞትን እንዲቀንስ ቢያስችልም ገና ብዙ ስራ እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል።
የማርቡርግ ወረርሽኝን ቶሎ በማወቅና በማሳወቅ ላብ ሪፖርት በማድረግ፣ መከላከያ በማሰማራት በተሰራው ስራ ሶስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መቆጣጠር አስችሎናል ይህም በጤናው ዘርፍ የተመዘገበ እመርታ ማሳያም ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ሀኪሞች በውጭ ያካበቱትን ልምዳና እውቀታቸውን ይዘው መጥተው መስራታቸው፣ከውጭ መጥተው የዓይንና የጥርስ ህክምናን በሐገር ውስጥ እንዲሰሩ በር መክፈቱን አብራርተዋል።
በዚህ መልኩ ለተሰማሩ መደገፍ ከእነሱ ጎን በመቆም የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ አድርገን እንዲሰፉ ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል።
ቨርቹዋል ሰርቪስ መስጠት የሚያስችሉ ተቋማት መገንባት የሚያስችል ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ልክ እንደ መሶብ ሲስተም ያለው ተሽከርካሪ ተሰርቶ በየሰፈሩ እየሄደ አገልግሎት መስጠት ይጀመራልም ብለዋል።
በሚካኤል ህሩይ