AMN – ጥር 27/2018 ዓ.ም
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በ10ኛ መደበኛ ስብሰባቸው ወቅት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ትንሳኤ፣ የብሔራዊ ጥቅምና የሰላም ጥሪን አስመልክቶ ለ ኤ ኤም ኤን በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ በግብርናና በኢንዱስትሪ ዘርፎች እያሳየች ያለው መነቃቃት የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻልና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር ቁልፍ ሚና እንዳለው አረጋግጠዋል።
የምክር ቤት አባሉ ከፈና ኢፋ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተለያዩ ሴክተሮች ከፍተኛ መነቃቃት እያሳየ ይገኛል። በተለይም፤ የግብርናው ዘርፍ ውጤታማነት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በፍጥነት እያደገ መሆኑን እና ይህ እድገት የኑሮ ውድነትን በማቃለልና ግሽበትን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።
ሀገሪቱ በምግብ ሰብል ራሷን ለመቻል የምታደርገው ጥረትም ተጨባጭ ውጤት እያሳየ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ ወ/ሮ አለሚቱ አበበ ኢኮኖሚው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀየረና የእድገት ጎዳና ላይ መሆኑን አንስተው፣ ቀጣዩን የ10.2 በመቶ እድገት ለማሳካት ርብርብ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ከማስከበር አኳያ አብረሃም አለማየሁ (ዶ/ር) መንግሥት በዲፕሎማሲና በባህር በር ጉዳይ የያዘው አቋም የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመዋል።
የባህር በር ጥያቄን በሰላማዊ መንገድ፣ በሰጥቶ መቀበልና በንግድ (Business Modality) መርሕ ለመፍታት የቀረበው አማራጭ ትክክለኛ መሆኑን አብራርተዋል። እያደገ የመጣው የኢኮኖሚና የሕዝብ ቁጥር የባህር በርን አስፈላጊነት አጉልቶታል ብለዋል።
ስለ ሰላም አስፈላጊነት አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ መስፍን እርካቤ፣ በሀገራዊ ጥቅምና በሰላም ጉዳይ ላይ ልዩነት ሊኖር እንደማይገባ አሳስበዋል።
ከጦርነት የሚገኘው አመድ ብቻ ነው ያሉት አቶ መስፍን፣ በማናቸውም ሁኔታ ያሉ ታጣቂ ኃይሎች መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ችግሮቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ አብዱጀሃድ መሃመድ በበኩላቸው፣ በኃይል የመነጋገርን መጥፎ ባህል በማስቀረት በብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን በኩል ሰላምን ለማውረድ በሚደረገው ጥረት እያንዳንዱ ዜጋ እንዲሳተፍ አሳስበዋል።
እንደራሴዎቹ በማጠቃለያቸው፣ የሀገር ምሰሶ የሆነውን ኢትዮጵያን የማቆየት ጉዳይ ድርድር የማይቀርብበት በመሆኑ፣ ለሰላምና ለልማት በጋራ መቆም እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ