በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነው ሰው አልባ የፖሊስ ጣቢያ ወደ ስራ ሊገባ ነው

You are currently viewing በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነው ሰው አልባ የፖሊስ ጣቢያ ወደ ስራ ሊገባ ነው

AMN- ጥር 27/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በቦሌ ክፍለ ከተማ፣ ሩዋንዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ያስገነባውን ዘመናዊና ሰው አልባ የፖሊስ ጣቢያ (Smart Police Station) ወደ ስራ ለማስገባት የመጨረሻ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑን ገልጿል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ከፍተኛ አመራሮችም በማዕከሉ ጉብኝት አድርገዋል።

በጉብኝቱ ወቅት የአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ምክትል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ሀሰን ነጋሽ፣ ይህ ጣቢያ አዲስ አበባ እንደ ስሟ የሚመጥን ቴክኖሎጂ እንድትታጠቅ እየተሰራ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።

ፖሊስ ከቴክኖሎጂ ጋር አብሮ እንደሚራመድ የታየበት ስራ ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስም በቀጣይ በተመረጡ ቦታዎች መሰል ጣቢያዎችን በመገንባት አገልግሎቱን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የፌደራል ፖሊስ የቴክኖሎጂ ኦፕሬሽን ዋና ክፍል ኃላፊ ኢንጅነር አንተነህ ሲሳይ፣ ጣቢያው በዓለም አቀፍ ደረጃ አራተኛ፣ በአፍሪካ ደግሞ የመጀመሪያው መሆኑን ለጎብኚዎቹ ገልጸዋል።

በዚህ ስማርት ጣቢያ ዜጎች ከሰው ንክኪ ነፃ በሆነ መልኩ በቴክኖሎጂ ታግዘው አቤቱታቸውን ማቅረብ ይችላሉ።

አገልግሎቱ በሰው አማካኝነት የማይሰጥ በመሆኑ፣ አልፎ አልፎ የሚሰሙ የሙስና እና የዲሲፕሊን ግድፈቶችን ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር መሆኑም ተመላክቷል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ አመራሮች ይህንን ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ወደ መሬት ማውረድ መቻሉ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይ ከክፍለ ከተማ እስከ ጣቢያ ድረስ ቦታዎችን በማመቻቸት መሰል የቴክኖሎጂ ማዕከላት እንዲስፋፉ እንደሚሰሩ ማረጋገጣቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ለኤ ኤም ኤን የላከው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review