ምልክት የማይታይበት፤ ዝምተኛው ገዳይ በሽታ

You are currently viewing ምልክት የማይታይበት፤ ዝምተኛው ገዳይ በሽታ
  • Post category:ጤና

AMN ጥር 28/2018 ዓ.ም

አብዛኛውን ጊዜ በሰውነታችን ውስጥ በዝምታ ተደብቆ የሚቆይ፣ ምንም አይነት ግልጽ የህመም ምልክት ሳያሳይ ጉበታችንን የሚያጠቃው ‘የጉበት ስብ’ (Fatty Liver) በዘመናችን ‘ዝምተኛው ገዳይ’ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

ብዙዎች በሽታው በውስጣቸው እንዳለ የሚያውቁት ጉዳቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ምርመራ ሲያደርጉ ብቻ ነው።

ይህንን አደገኛ ሁኔታ አስቀድሞ መከላከልና መመለስ የሚቻልባቸው መንገዶች አሉ የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን ፈቃዴ፣ ስለ ጉበት ስብ መንስኤዎችና መከላከያ መንገዶች ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የጉበት ስብ ወይም በህክምና መጠሪያው ‘ፋቲ ሊቨር’ (Fatty Liver) የምንለው የጤና ችግር፣ በጉበታችን ውስጥ መገኘት ከሚገባው በላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ስብ ሲከማችና በጉበት ስራ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሲያሳድር የሚከሰት ነው።

ብዙዎቻችን ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ምልክት ስለማያይ በዝምታ የምንጠቃበት ይህ የጤና እክል፣ በአግባቡ ካልተያዘ ለከፋ የጉበት ጉዳት ሊዳርግ ይችላል ብለዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን ከኤኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የጉበት ስብ አይነቶችና መንስኤዎቻቸው ሲያስረዱ የጉበት ስብ በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ሊከሰት ይችላል ብለዋል እነዚህም፤

በአልኮል ምክንያት የሚመጣ የጉበት ስብ

ከፍተኛ መጠን ያለው አልኮል ለረጅም ጊዜ በመጠጣት የሚከሰት የጉበት ጉዳት ነው።

ከአልኮል ውጭ የሚመጣየጉበት ስብ

ከአልኮል መጠጥ ውጭ በአመጋገብና በሌሎች የጤና እክሎች ምክንያት የሚከሰት ሲሆን፣ ዋና ዋና መንስኤዎቹም፦

የስኳር በሽታ፦ የስኳር ታካሚዎች በደማቸው ውስጥ ያለውን ግሉኮስ መቆጣጠር ሲያቅታቸው፣ ጉበት ትርፍ ግሉኮስን ወደ ስብ በመቀየር በውስጡ እንዲከማች ያደርጋል።

የኮሌስትሮል መዛባት፦ በሰውነታችን ውስጥ መጥፎ ኮሌስትሮል (LDL) እና ትራይግላይሰራይድ ሲጨምር እንዲሁም ጥሩው ኮሌስትሮል (HDL) ሲቀንስ ለጉበት ስብ እንጋለጣለን።

የተሳሳተ አመጋገብ፦ ፋይበር የሌላቸውና የተቀነባበሩ ምግቦች፣ ከፍተኛ ስኳር ያላቸው መጠጦች፣ እና በዘይት የተጠበሱ (እንደ ቺፕስና ቦምቦሊኖ ያሉ) ምግቦች ዋነኛ ተጠያቂዎች ናቸው።

የጉበት ስብ ትልቁ አደጋ ምንም አይነት የህመም ምልክት አለማሳየቱ ነው።

ማንኛውም ሰው ተመርምሮ እስካላረጋገጠ ድረስ በሽታው በውስጡ መኖሩን ላያውቅ ይችላል ብለዋል።

በተለይ ደግሞ የደም ግፊት፣ ስኳር እና የኮሌስትሮል ችግር ያለባቸው ሰዎች ለዚህ ችግር ይበልጥ ተጋላጭ ስለሆኑ በየጊዜው ምርመራ እንዲያደርጉ ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉቀን ይመክራሉ።

ተፈጥሯዊ መፍትሄዎችና የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ

የጉበት ስብን በምግብ ስርዓትና በአኗኗር ዘይቤ ለውጥ ሙሉ በሙሉ ማከም እንደሚቻል እና ለዚህም የሚከተሉትን ነጥቦች መተግበር ይገባል ብለዋል።

ጤነኛ ቅባቶችን መጠቀም፦ እንደ አሳ፣ ተልባ፣ ሰሊጥ፣ አቮካዶ እና የወይራ ዘይት ያሉ ‘ኦሜጋ 3’ (Omega 3) የበለጸጉ ጤነኛ ቅባቶችን ማዘውተር።

ያልተፈተጉ የእህል ዘሮችን መመገብ፦ እንደ ገብስ፣ አጃ፣ ስንዴ፣ ባቄላና ምስር ያሉ የፕሮቲንና የፋይበር ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑ ምግቦችን መጠቀም።

ከመጥፎ ቅባቶች መራቅ፦ በሙቀት አካባቢ የሚረጉ ቅባቶችን (እንደ ጮማ ስጋ፣ ቅቤና የሚረጋ ዘይት) እንዲሁም ‘ትራንስ ፋት’ ያላቸውን የተጠበሱ ምግቦች ማስወገድ።

አካላዊ እንቅስቃሴ፦ መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግና አልኮልን ሙሉ በሙሉ ማቆም ለጉበት ጤና ወሳኝ ናቸው።

ጤናዎን ለመጠበቅ የምግብ ስርዓትዎን ከማስተካከል ጎን ለጎን የህክምና ባለሙያ ማማከርን አይርሱ።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review