AMN – ጥር 28/ 2018 ዓ.ም
የመምህራን የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ በይፋ መጀመሩ፣ መምህራን በየወቅቱ ሲያነሷቸው ለቆዩት ዘመናዊና መሠረታዊ ጥያቄዎች ትልቅ ምላሽ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ መምህራን ማህበር አስታወቀ።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ድንቃለም ቶሎሳ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ማህበሩ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከሚሰራው ስራ ጎን ለጎን የመምህራን ጥቅማጥቅም እንዲከበርና ሙያዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ በትኩረት ሲሰራ ቆይቷል።
በዚህም መሠረት ለከተማ አስተዳደሩ ሲቀርቡ ከነበሩ የጥቅማጥቅም ጥያቄዎች መካከል አብዛኛዎቹ ምላሽ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንቱ እንደ ማሳያ የጠቀሱት የቤት ኪራይ አበል ማሻሻያውንና የትራንስፖርት አገልግሎትን ነው።
መምህራን የመማር ማስተማር ስራቸውን በአግባቡና በሰዓቱ እንዲወጡ ለማስቻል፣ የከተማ አውቶቡስና የሸገር ትራንስፖርትን በነፃ እንዲጠቀሙ መደረጉን አስታውሰዋል።

በተጨማሪም በ2009 ዓ.ም በቅናሽ ዋጋ ተላልፈው የነበሩ ቤቶች፣ በ2014 ዓ.ም በከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ መምህራን በስማቸው እንዲያዘዋውሩ መደረጉን ገልጸዋል።
አሁን ላይ የተጀመረውን ሰፊ የቤት ግንባታ በተመለከተ አቶ ድንቃለም ሲያስረዱ፤ የከተማ አስተዳደሩ ለመምህራን ልዩ ትኩረት በመስጠት 40 ሄክታር መሬት ከሊዝ እና ከካሳ ክፍያ ነፃ በሆነ መንገድ ማስረከቡን ተናግረዋል።
አስተዳደሩ ለባለመሬቶች የካሳ ክፍያ መክፈሉም ግንባታው ያለ ምንም እንቅፋት እንዲጀመር መንገድ ከፍቷል ብለዋል።
የመክፈል አቅምን ከግምት ውስጥ ያስገባ አዲስ አሰራር መዘርጋቱንም የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ ቀደም ሲል የነበረው የ30/70 የቤት ቁጠባ አሰራር ለመምህራን ወደ 25/75 እንዲሻሻል መደረጉንና መምህራንም ተደራጅተው በመቆጠብ ላይ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ይህ ሁሉ ጥረት መምህሩ ተረጋግቶ የማስተማር ስራውን እንዲያከናውንና ነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎችን በአግባቡ እንዲያፈራ በማሰብ መሆኑን አቶ ድንቃለም ቶሎሳ አክለው ገልጸዋል።
በአስማረ መኮንን