AMN – ጥር 28 ፣ 2018
ኢትዮ ቴሌኮም፣ ከጅቡቲ ቴሌኮም እና ሱዳቴል ግሩፕ ጋር የ“ሆራይዘን” ድንበር ተሻጋሪ የፋይበር መስመር ዝርጋታን እውን ለማድረግ የሚያስችል የሦስትዮሽ ስምምነት ፈጸመ።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ “በኢትዮ ቴሌኮም፣ በጅቡቲ ቴሌኮም እና በሱዳቴል ግሩፕ መካከል የተደረገው ይህ የሦስትዮሽ ስምምነት፥ የጋራ የዲጂታል የወደፊት ዕጣ ፈንታችንን ለመገንባት የሚያስችል ነው” ብለዋል።
የሆራይዘን ፋይበር ኢኒሼቲቭ ጠንካራና ከፍተኛ አቅም ያለው እንዲሁም አፍሪካን በዲጂታል የሚያስተሳስር የኮኔክቲቪቲ ኮሪደር ለመፍጠር የተወሰደ ወሳኝ እርምጃ መሆኑንመም ገልጸዋል፡፡
ስምምነቱ የጅቡቲን የባሕር ውስጥ የፋይበር ኬብሎች በኢትዮጵያ በኩል አድርጎ ከሱዳን ጋር በማስተሳሰር፥ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ትስስርን የሚያጠናክር፥ አስተማማኝ የፋይበር መስመር ዕውን እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የዲጂታል መሠረተ ልማት ሀብቶቻችንን፣ ቴክኒካዊ ክህሎቶቻችንን እና የጋራ ራዕያችንን በማቀናጀት፤ የአፍሪካ ኦፕሬተሮች ተጨባጭ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እንዲሁም ለደንበኞቻችን እና ለግዙፍ የዳታ ኩባንያዎች አዲስ እሴት ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ሀገራትን በትብብር የሚያስተሳስር፣ ኢኮኖሚን የሚያጠናክር እና ቀጣናውን በዓለም አቀፍ የዲጂታል ሥነ-ምሕዳር ውስጥ ጠንካራ እና አስተማማኝ ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት ማስተላለፊያ (Gateway) የሚፈጥር ስለመሆኑ አብራርተዋል።
የጅቡቲ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር መሐመድ አሶዌ ቡህ በበኩላቸው፤ “የሆራይዘን ፕሮጀክት ለአገራቱ የጋራ ዕድገትና ብልጽግና ያለንን ራዕይ መሠረት በማድረግ በቀጠናው የቴሌኮም መሠረተ ልማትና ትስስር አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው” ብለዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው የዲጂታል ሉዓላዊነትን በማጠናከር ቀጠናው በዓለም አቀፍ መድረክ ያለውን ሚና የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሱዳቴል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ማግዲ ኤም. አብደላ ታሃ በበኩላቸው፥ “የሆራይዘን ፕሮጀክት ከመሠረተ ልማት ግንባታነት ባሻገር በአፍሪካ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች መካከል ለሚደረግ የፈጠራ አጋርነት ሕያው ምስክር ነው” ማለታቸውን ኢትዮቴሌኮም በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።