AMN ጥር 29/2018 ዓ.ም
ለዓመታት የአዲስ አበባ ወንዞች አፍንጫን በሚሰነፍጥ ሽታ እና ለዕይታ በማይስብ የቆሻሻ ክምር ተሞልተው መቆየታቸው ይታወቃል።ዛሬ ግን ያ ታሪክ ተቀይሮ ወንዞቹ አዲስ መልክ ተጎናጽፈው ወደ ዘመናዊ የመዝናኛ ማዕከልነት እየተቀየሩ ይገኛሉ።
በተለይም የፒኮክ መናፈሻ እና አካባቢው ያስመዘገበው ለውጥ፣ ተፈጥሮን ከዘመናዊነት ጋር በማጣመር ለአካባቢው ነዋሪዎችና ለወጣቶች አዲስ ተስፋን ይዟል። የቆሻሻ ማከማቻ የነበረው ስፍራም ዛሬ ወደ ውበት ማዕከልነት ተለውጧል።
እየተካሔደ የሚገኘው የልማት ሥራ የአካባቢውን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለበርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል መፍጠሩን የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚዎች ይመሰክራሉ።

የአካባቢውን የቀድሞ ሁኔታ ያስታወሱት አቶ ዓለማየሁ ኃይሉ፣ ይህ ቦታ ቀደም ሲል በጣም የሚሸት፣ ቆሻሻና ሊወድቁ የደረሱ ቤቶች የተከማቹበት መንደር ነበር፤ ወንዙም አሁን ካለበት መስመር ወጥቶ በመሃል ይፈስ ነበር ይላሉ። አሁን ግን ቦታው ጸድቶና ልማቱ ተጠናቆ ሲታይ ያለው ልዩነት በፍጹም የማይገናኝ ን ነው ብለዋል።
ይህ የወንዝ ዳርቻ ልማት ለውበት ብቻ ሳይሆን ለብዙዎች የሥራ ዕድል፥ የዜጎች ተጠቃሚነት እና የኑሮ ዋስትና ሆኗል የሚሉት አቶ ዓለማየሁ፤ በፊት በየጎዳናው ሲያድሩ የነበሩ ወጣቶች ዛሬ እዚህ መጥተው የቀን ውሏቸውን ሸፍነው ቤተሰቦቻቸውን እያስተዳደሩበት ይገኛሉ።
ሌላው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ አቶ ታደሰ ግርማ፣ ወንዙ ቀደም ሲል የቆሻሻ መጣያና መጸዳጃ ሆኖ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ያለው ንጽሕና ግን አስደሳች መሆኑን እና ተፈጥሮን ከዘመናዊነት ጋር ያጣጣመ እንደሆነ ገልጸዋል።

የአትክልትና ፍራፍሬ አልሚ ድርጅት ሥራ አስኪያጁ አቶ ተስፋዬ ዶራ በበኩላቸው የፒኮክ ፓርክን የቀድሞና የአሁኑን ሁኔታ ሲያነጻጽሩ ለውጡ እጅግ አስገራሚ መሆኑን ይናገራሉ። በሠራነው ሥራ ራሳችን ተዝናንተንና ተደስተን እንገኛለን በማለት የሥራውን ውጤታማነት ገልጸዋል።
በተመሳሳይ አቶ ተስፋዬ መስፍን፣ ልማቱ የዘመነ መሆኑንና ብዙ ወጣቶች ሌሊት እስከ ስድስት እና ሰባት ሰዓት ድረስ በመስራት ሙያ እንደቀሰሙበት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ዛሬ የፒኮክ መናፈሻና አካባቢው ተፈጥሮን ያጣጣመና ዘመናዊነትን በውል የገለጠ ሆኗል። በርካታ ኢትዮጵያውያንም የማይነጥፍ ሥራቸውንና አሻራቸውን በማሳረፍ ቦታው የከተማዋ አዲስ የለውጥ ተምሳሌት ሆኗል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ