የእንቅርት በሽታ መንስኤዎች፣ ምልክቶችና የሕክምና አማራጮች

You are currently viewing የእንቅርት በሽታ መንስኤዎች፣ ምልክቶችና የሕክምና አማራጮች
  • Post category:ጤና

AMN – ጥር 29/2018 ዓ.ም

በአንገት ላይ በሚገኝ የታይሮይድ እጢ እብጠት የሚታወቀው የእንቅርት በሽታ (Goiter)፣ በአመጋገብ ሥርዓት መዛባትና በሆርሞን ለውጦች ምክንያት እየተስፋፋ መሆኑን የጤና መረጃዎች ያመላክታሉ።

በየካቲት 12 ሆስፒታል የጠቅላላ ቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር የአብሥራ መኮንን እንደገለጹት፣ ለበሽታው መከሰት ዋነኛው መንስኤ የአዮዲን ንጥረ-ነገር እጥረት ነው።

የታይሮይድ እጢ በቂ ሆርሞን ለማምረት የአዮዲን ግብዓት የሚጠቀም ሲሆን፣ ይህ ንጥረ-ነገር በሚታጣበት ጊዜ እጢው ያለበትን ክፍተት ለመሙላትና በቂ ሆርሞን ለማምረት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። በዚህ ሂደት ውስጥም የእጢው መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር ለዕብጠት ይዳረጋል።

ዶ/ር የአብሥራ አክለውም እንደገለጹት፣ ከአዮዲን እጥረት በተጨማሪ እንደ ግሬቭስ እና ሀሺሞቶ ያሉ የሰውነት በሽታ የመከላከል ሥርዓት መዛባቶች እጢው ከመጠን በላይ ሆርሞን እንዲያመነጭ ወይም እንዲያንስ በማድረግ ለእንቅርት መከሰት ትልቅ ድርሻ አላቸው።

ከዚህም ባለፈ በእርጅና፣ በጉርምስና፣ በእርግዝና እና በማረጥ ወቅት የሚከሰቱ ተፈጥሯዊ የሆርሞን መለዋወጦች ለበሽታው ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ሲሆን፤ በእጢው ላይ የሚወጡ ትናንሽ ጓጎሎች፣ የዘር ውርስ እና ለተለያዩ የጨረር አይነቶች መጋለጥ ለበሽታው መከሰት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።

ሕመሙ መጀመሪያ ላይ ምንም አይነት ግልጽ ስሜት ላይኖረው ቢችልም እብጠቱ እየጨመረ ሲመጣ ግን በአንገት ስር በግልጽ የሚታይ እብጠት እንደሚፈጠር ዶ/ር የአብሥራ ገልፀው፤ ይህን ተከትሎ የድምፅ መጎርነን ወይም የድምፅ መቀየር፣ በተለይም በጀርባ በሚተኙበት ወቅት የመታፈን ስሜት፣ ተደጋጋሚ ሳል እና ምግብ ለመዋጥ መቸገር የመሳሰሉ ምልክቶች ይስተዋላሉ።

እብጠቱ በከፍተኛ ደረጃ ሲያድግም በታካሚው ላይ ከባድ የመተንፈስ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ባለሙያው አስረድተዋል።

ለበሽታው መፍትሄ ለማግኘት በመጀመሪያ ደረጃ የደም ምርመራ እና የአልትራሳውንድ ምርመራ በማድረግ የእብጠቱን አይነትና መንስኤ ማወቅ ያስፈልጋል። እንደ ምርመራው ውጤትም በአዮዲን የበለፀጉ እንደ አዮዲን ያለበት ጨው እና የባህር ምግቦችን በአግባቡ በመጠቀም የአመጋገብ ሥርዓትን ማስተካከል ይገባል።

በተጨማሪም የሆርሞን መዛባትን ለማስተካከል የሚረዱ መድኃኒቶችን መጠቀም፣ ከመጠን በላይ ሆርሞን የሚያመነጭ እጢን በሬዲዮ አክቲቭ አዮዲን ማክሰም ወይም እብጠቱ የመተንፈስና የመዋጥ ችግር ሲፈጥር በቀዶ ጥገና የማስወገድ ሕክምናዎች እንደሚሰጡ ዶ/ር የአብሥራ መኮንን ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ አስገንዝበዋል፡፡

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review