AMN – ጥር 29/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባዔዉን በአድዋ ድል መታሰቢያ የምክር ቤቱ አዳራሽ ማካሄድ ጀምሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩን የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትን ለምክር ቤቱ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።
በዚህም ወደ ከተማዋ የሚመጡ ቱሪስቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እየጨመረ ይገኛል።

ባላፉት ስድሰት ወራት 4 ነጥብ 7 ሚሊየን የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ከተማዋን ይጎበኛሉ ተብሎ ታስቦ የነበረ ቢሆንም ከዕቅድ በላይ 4 ነጥብ 9 ሚሊየን ቱሪስቶች መዲናዋን መጎብኘት ችለዋል ሲሉ በሪፖርታቸው ገልጸዋል።
ለዚህም በከተማዋ ላይ ሲከበሩ የነበሩ ሕዝባዊ፥ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ የአደባባይ በዓላት፥ እንዲሁም የስፖርትና የጤና ቱሪዝም መስፋፋት ከፍተኛ አበርክቶ ነበራቸው ብለዋል።
በተመሳሳይ 699 ሺህ 761 የውጭ ቱሪስቶች ከተማዋን ለመጎብኘት የቻሉ ሲሆን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ15 በመቶ ብልጫ አሳይቷል ብለዋል።

ከተማዋን የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ያከናወናቸው በርካታ የልማት ስራዎችና ሜጋ ፕሮጀክቶች ፍሬ በማፍራት በከተማዋ ውስጥ የሚደረጉ ኩነቶች እንዲጨምሩ ማስቻሉን ገልጸዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት 150 የሚሆኑ ዓለም አቀፍና አሕጉር አቀፍ ኩነቶች አዲስ አበባ ላይ የተካሄዱ ሲሆን ይህም የ50 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ጨምረው ገልጸዋል።
በዚህም የተነሳ ከሀገር ውስጥ እንዲሁም ከውጪ ሀገር የቱሪስት ፍሰት ባለፉት ስድስት ወራት 155 ቢሊየን ብር ወደ ኢኮኖሚው ፈሰስ መሆን መቻሉን ተናግረዋል።
በሚካኤል ኅሩይ