በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የስፖርት ፓርክ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

You are currently viewing በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የስፖርት ፓርክ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

AMN – ጥር 29/2018 ዓ.ም

በካዛንቺስ የመልሶ ማልማት በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነና የተለያዩ ዘመናዊ እና ባሕላዊ ስፖርቶችን ማስተናገድ የሚችል የስፖርት ፓርክ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባዔዉን ባከናወነበት ወቅት ባለፉት ስድስት ወራት በስፖርት ልማት የተሠሩ ተግባራትን ሪፖርት አድርገዋል።

ከንቲባዋ በሪፖርታቸው በስድስት ወራት ውስጥ የእግርኳስ፣ የመሮጫ መም፣ሦስት በአንድ ሜዳ፣ ሁለት በአንድ ሜዳ እና የስኬት ቦርድን ያካተቱ 32 የስፖርት ማዘውተሪያዎች መገንባታቸውን አንስተዋል፡፡ በካዛንቺስ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው የስፖርት ፓርክ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ እንደሆነም ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡

ከስልጠና ጋር በተያያዘ በ723 የስልጠና ጣቢያዎች በ20 የስፖርት ዓይነቶች በክረምት እና በበጋ 84,683 አዳጊ ወጣቶች ስልጠና ማግኘታቸውን አንስተዋል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከወከሉ 25 ተጫዋቹች 17ቱን ማስመረጥ መቻሉን ከንቲባ አዳነች በሪፖርታቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡

የማሕበረሰብ አቀፍ ስፖርትን በተመለከተም በአጠቃላይ 3.2 ሚሊየን ሰዎች በሚኖሩበት፣ በሚሠሩበትና በሚዝናኑበት አካባቢ ተሳታፊ እንዲሆኑ መደረጉን በሪፖርታቸው ገልጸዋል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review